Fana: At a Speed of Life!

ለመኸር እርሻ  የሚውል 9 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ገብቷል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 12 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለመኸር እርሻ የሚውል 9 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለመደገፍ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መመደቡም ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ እንደገለጹት÷ ለዘንድሮ የመኸር እርሻ 18 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ግዥ እየተካሔደ ነው።

በዚሁ መሰረት ጂቡቲ ወደብ ከደረሰው 10 ሚሊየን ኩንታል ውስጥ 9 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ አገር ውስጥ ገብቶ ወደ ዩኒየኖች መጋዘን መድረሱን ገልፀዋል።

የማዳበሪያ ግዥውን ለመፈፀም ቀድሞ ጨረታ የወጣ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝና ሌሎች ምክንያቶች የዋጋ ጭማሪ ማጋጠሙን ጠቁመው÷ የዋጋ ጭማሪው በአርሶ አደሩ ላይ ጫና እንዳያሳድር ዘንድሮ የሚካሔደውን የግብዓት ግዥ ጨምሮ ዘርፉን ለማነቃቃት መንግስት ከ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

የማዳበሪያ ዋጋ የአርሶ አደሩን አቅም ያገናዘበ እንዲሆን ጨረታውን ካሸነፉ ድርጅቶች ጋር ድርድር ተደርጎ የ945 ሚሊየን ብር ቅናሽ እንዲኖር ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ከ10 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በዓመት 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ይውል እንደነበረ አስታውሰው ÷ በ2012/13 የምርት ዘመን 14 ሚሊየን ኩንታል መድረሱን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ለዘንድሮ የምርት ዘመን 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንና በእስካሁን ሒደት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል በመሰብሰብ የዕቅዱ 73 በመቶ ላይ እንደተደረሰ ጠቁመዋል።

የተባይና የሰብል በሽታ ክስተትን ለመከላከል የሚውል 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሊትር ኬሚካል በግዥ ሂደት ላይ እንደሚገኝም አክለዋል።

ዘንድሮ የሚቀርበው ማዳበሪያ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ24 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ እንዳለው ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት በመጪው ሰኔ ማገባደጃ እንደሚጠናቀቅም  ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.