Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑክ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 12 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
ልዑኩ በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሰሜን ካሊፎርኒያ ኔቫዳና አሪዞና ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ምግባረ ሠናይ ድርጅት ዋና ሰብሳቢ የተመራ መሆኑ ተመላክቷል።
በውይይታቸው ልዑኩ በትግራይ እንዲሁም በቤንሻንጉል ክልሎች ለተከሰቱ ችግሮች ድጋፍ ለማድረግ በሰሜን አሜሪካ ሀገረ ስብከት ስር ከሚገኙ ምዕመናን በምግባረ ሠናይ ድርጅቱ አማካኝነት የተሰበሰበ እርዳታ ይዞ መምጣቱን ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ገልፀዋል።
ብፁዕነታቸው አያይዘውም በዋሽንግተን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ለተደረገላቸው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
የዋሽንግተን ዲሲ አካባቢው ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ስዩማን ቀሲስ ጥላሁን አበበ በበኩላቸው÷ በአሜሪካና በካናዳ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በተናጠል ያደርጉት የነበረውን የልማት ስራዎች ወደ አንድ በማምጣት ከ350 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ መሰብሰቡን ገልፀዋል።
ድጋፉ ለማድረስ ይቻል ዘንድ ከ60 ዓመታት በላይ በምግባረ ሰናይ ስራዎች ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ በቆየው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ልማትና ክርስቲያናዊ ተረድኦ ኮሚሽን በኩል ለመፈጸም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በበኩላቸው÷ ዲያስፖራውን በማስተባባር ለተሰበሰበው እርዳታ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
እርዳታውን ለማድረስ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የሚጠበቀውን ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ጽዮን አያይዘውም በቀጣይም ቤተከርስቲያኗ ዳያስፖራውን በማስተባበር በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽኅፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.