Fana: At a Speed of Life!

ከሰሞኑ ሱዳን 61 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዛ ለቃለች በሚል የሚናፈሰው ወሬም ከእውነት የራቀ እና ፍጹም ሃሰት ነው- አምባሳደር ዲና

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከኢትዮ ሱዳን የድንበር ጉዳይ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ለሰላማዊ መፍትሔ ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከሰሞኑ ሱዳን 61 የኢትዮጵያ ወታደሮችን ይዛ ለቃለች በሚል የሚናፈሰው ወሬም ከእውነት የራቀ እና ፍጹም ሃሰት መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

በሱዳን ተይዘው የነበሩት 59 አርሶ አደሮች እና 2 ሚሊሻዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ሠላማዊ መንገድን ብቻ አማራጭ በማድረግ የሁለቱ ሀገራት የድንበር ጉዳይ በሰላም እንዲፈታ ትሻለች፤ ጥረቷንም ትቀጥላለችም ብለዋል።

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘም ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብ ድርድር ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣ የሚያደርጉት ጥረት በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አንስተዋል።

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እየተካሄደ ባለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት ኢትዮጵያ በማይናወጥ አቋሟ መቀጠሏን ገልጸው ግብፅና ሱዳን ግን ጉዳዩ ከህብረቱ አደራዳሪነት እንዲወጣ እየጣሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ እንደጻፈች መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሶስትዮሽ ድርድሩ ግብፅና ሱዳን ጉዳዩ ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣ ጫና እያደረጉ በመሆናቸው ምክር ቤቱ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ እንዲያደርግ በደብዳቤው ተመልክቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፈታት ይችላል የሚል የፀና አቋም ስላላት የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል እየሰራች መሆኑን አረጋግጠዋል።

ግብፅና ሱዳን የድርድር ሂደቱን ከአፍሪካ ህብረት ለማስወጣት የሚያደርጉ ጥረት በኢትዮጵያ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለውም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.