Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰሩ መሆኑን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፤ ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የሃገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ መወሰን የሚያስችል በመሆኑ ህብረተሰቡ የምርጫ ካርድ በመውሰድ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው እንደጠቆሙት፤ “በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ጠንካራ እና በህዝብ ይሁንታ የተቋቋመ መንግሥት መመስረት ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡

በጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ አልያም ከአካባቢያቸው ወደ ሌላ ቦታ የተንቀሳቀሱ ዜጎች መኖራቸውን ተከትሎ በምዕራብ ኦሞ ዞን እና በቤንች ሸኮ ዞን በስድስት ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ ላይካሄድ እንደሚችልም ነው የተናገሩት፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ምርጫው ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት በሁሉም አካባቢዎች የምርጫ ጣቢያዎች ክፍት ሆነው መራጮች በነፃነት ምዝገባ እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለፃ፤ በተለይ ከዚህ በፊት አልፎ አልፎ ግጭቶች ይስተዋሉባቸው የነበሩ የአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች አዋሳኝ አካባቢዎችን አስተማማኝ ሠላም የሰፈነባቸው ለማድረግ የዕርቀ ሠላምና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሥራዎች በስፋት ተሰርተዋል፡፡

የተሰራው ስራ የህዝቦችን አብሮነት ከማጠናከር ባለፈ ቀደም ሲል ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን በመመለስ ወደ አምራችነት መመለስ ማስቻሉን የደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.