Fana: At a Speed of Life!

አልጀሪያ እና ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎታቸውን ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አልጀሪያ እና ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ገለፁ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በኢትዮጵያ ከአልጀሪያ አምባሳደር ራቻድ ቢሎንስ ጋር መክረዋል።

አቶ ታገሰ ጫፎ ሁለቱ ሃገራት የቆየ የወዳጅነት ታሪክ እንዳላቸው መግለፅ፤ ግንኙነቱ በፖለቲካዊ ትብብር ሳይገድብ፣ በምጣኔ ሃብታዊ እና በማሕበራዊ ዘርፎችም ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት፡፡

የምጣኔ ሃብት አድማሱን ለማስፋት እና የሁለቱ ሀገራት የንግዱ ማሕበረሰብ በጋራ የሚሰሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ አልጀርስ በረራ እንዲኖረውም አፈ-ጉባኤው ከአምባሳደሩ ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ በፓን-አፍሪካ ፓርላማ ዙሪያ ከአምባሳደር ራቻድ ጋር የተወያዩ ሲሆን፣  ተቋሙ ተጠናክሮ የተሻለ አመራር እንዲኖረው ለማድረግ ሀገራቱ ከምርጫ በኋላ በጋራ እንደሚሰሩ አብራርተዋል፡፡

የአልጀሪያ አምባሳደር ራቻድ ቢሎንስ በበኩላቸው  የሁለቱን ሀገራት ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ትብብር ለማጠናከር ሀገራቸው እንደ ቀድሞው ሁሉ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡

አልጀሪያ በመጪው ሰኔ 19 ብሔራዊ ምርጫ እንደምታካሂድ የተናገሩት አምባሳደሩ፤ ሀገራቸው ከምርጫው በኋላ የፓን-አፍሪካ ፓርላማን እና አመራሩን ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ እንደምትሰራ ነው የተናገሩት ፡፡

በተመሳሳይ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ  ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒታን ጋር የሁለቱን ሀገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ተወያይተዋል፡፡

ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት መልካም ግንኙነት ለማጎልበት በንግድና ኢኮኖሚ፣ በመሰረተ-ልማት፣ በኢንቨስትመንት እና በጸጥታው ዘርፍ ከደቡብ ሱዳን ጋር ትኩረት ሰጥታ መስራት እንደምትፈልግ አስረድተዋል፡፡

ወንጀልን በጋራ በመከለላከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የበለጠ ለማሳደግ ሁለቱ ሀገራት በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም ዶክተር ነገሪ መግለፃቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ሀገራትን በማይጎዳ መልኩ ህዳሴ ግድቡን እየገነባች እና ተፈጥሮአዊ መብቷን ለመጠቀም ጥረት እያደረገች መሆኑን የገለጹት ዶክተር ነገሪ ሱዳን እና ግብጽ የሚያነሱትን ቅሬታ በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚያመነጨው ኃይል ለምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የተናገሩት ዶክተር ነገሪ፤ ግድቡ የኢትዮጵያ እና የደቡብ ሱዳን ገጠራማ አካባቢዎችን በኤሌክትሪክ ተደራሽ እንደሚያደርግ ተስፋ ተጥሎበታልም ብለዋል፡፡

ዶክተር ነገሪ በተጨማሪ በህዳሴ ግድቡም ሆነ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የሚስተዋለውን የድንበር ይገባኛል ውዝግብ በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት መንግስት ሁለንተናዊ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒታ በበኩላቸው ደቡብ ሱዳን እንደ አገር ስትመሰረት ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር የበኩሏን ድጋፍ ማድረጓን ያስታወሱት አምባሳደር ጀምስ፣ አሁንም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ተማሪዎች ስኮላርሺፕ በመስጠጥና ፖሊስ በማሰልጠን ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ወንጀልን በጋራ ለመከላክል እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያ ዜጎች የመታወቂያ ወረቀት እየሰጠች እንደሆነም አምባሳአደሩ ገልጸዋል፡፡

በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ሱዳን እና ግብፅ የሚያሳዩት ተቃውሞ እና አለመግባባት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት መፈታት እንዳለበት እና ኢትዮጵያም ጥቅሟን ለማስከበር ለድርድሩ ዝግጁ መሆን እንዳለባት አምባሳደር ጀምስ አሳስበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.