Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር አለምፀሃይ መሰረት ከኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኡጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር  አለምፀሃይ መሰረት ከዩጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ኦርየም ኦከሎ ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን የመልሶ ማቋቋም እንቅሰቃሴ እና የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ሂደትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት የግድቡ የግንባታው አካል በመሆኑ በእቅዱ መሰረት እንደሚቀጥል፣ ኢትዮጵያ የሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌትን በተመለከተ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ለሁለቱም የታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ጥሪ ማቅረቧን እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት  እየተካሄደ ያለው የሶስትዮሽ ድርድር መፍትሄ እንደሚያመጣ በጽኑ እንደምታምን አምባሳደር አለምጸሀይ አስረድተዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው በበኩላቸው በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ-ማስከበር ዘመቻ በአጭር ጊዜ ማለቁን  በበጎ ጎን ማየታቸውን ገልጸው÷ በክልሉ ከሰብአዊ ቀውስና ሌሎች ተያያዥ ተግዳሮቶች የሚጠበቁ መሆናቸውን  ተናግረዋል፡፡

ለጉዳዩም መንግስት መፍትሄ ለመስጠት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ ሚኒስትር ዲኤታው ኡጋንዳ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የሆነ የአባይ ውሃ ተጠቃሚነትን በተመለከተ  የናይል አጠቃላይ ስምምነት ማዕቀፍን በመፈረም ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየቷን አስታውሰዋል።

አሁንም በአባይ ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ የፀና አቋም እንዳላትና የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ተቀባይነት እንደሌላችውም አስረድተዋል፡፡

አያይዘም  ማንኛውም የተፋሰሱ አባል ሀገር ከአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት እንዳለውና ይህም መከበር እንደሚገባው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ  የምትገነባው ግድብ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር በቀጠናው ያለውን ዝቅተኛ የሆነ የሃይል አቅርቦት ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።

ከፍተኛ ውሃ ከቪክቶሪያ ሀይቅና ከኡጋንዳ ግድቦች ካለፈው አመት ጀምሮ እየፈሰሰ እንደሚገኝ በመግለፅ ÷ በዚህም ከፍተኛ የውሃ መጠን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዳገኙ፣ ዘንድሮም ከፍተኛ ዝናብ ይኖራል ተብሎ ስለሚጠበቅ የውሃ እጥረት እንደማያጋጥም ጠቁመል።

የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.