Fana: At a Speed of Life!

የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ 907 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለሚተገበሩ ሶስት ፕሮጀክቶች 907 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት አድርጓል።

ስምምነቱ በኢትዮጰያ መንግስት እና በዓለም ባንክ የ907 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ የተፈረመ ሲሆን፤ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴና የዓለም ባንክ ግሩፕ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ሶስት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ይውላል፡፡

ከድጋፉ 200 ሚሊየን ዶላሩ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የሚውል ሲሆን፤ ኢንተርፕራይዞች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለደረሰባቸው ተጽዕኖ ቢደገፉ በስራቸው አዋጭ ሆነው ለመቀጠልና በንግድ ውስጥ እንዲቆዩ የሚያስችል ነው፡፡

500 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ተደራሽነት ከማሳደግ ባሻገር የግሉ ዘርፍ ካፒታል ተሳትፎን እና ዘላቂ የፋይናንስ አማራጮችን ለማምጣት የሚያስችል አካባቢን ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡

የ207 ሚሊየን ዶላር ስምምነቱም በኢትዮጵያ ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከተለውን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም የበሽታው መከላከያ ክትባቶችን ውጤታማ እና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲዳረስ ለማድረግ የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ መሆኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ስምምነቱ የተፈረመው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው እና የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማስፋፊያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በተገኙበት ነው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.