Fana: At a Speed of Life!

ቅዱስ ጊዮርጊስ ጌታነህ ከበደ ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለምን ከዋናው ቡድን አገደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለም መስፍንን ከፍተኛ የስነ ምግባር ግድፈት በመፈፀማቸው ከዋናው የእግር ኳስ ቡድን ማገዱን አስታወቀ።

የቅዱስ ጊዮርስ ስፖርት ማህበር ባወጣው መግለጫ በ2013 ዓ.ም በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን የስራ አመራር ቦርዱ ባለው አቅም ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ቡድኑ እየተደረገለት ካለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አንጻር የሚጠበቅበትን ያህል አርኪ የሚባል እንቅስቃሴ እያደረገ እንዳልሆነ ነው የገለፀው።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፎ አልፎ በቡድኑ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ተጫዋቾች የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪና የስነ-ምግባር ጉድለት እንዳሳሰበው ማህበሩ በፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጠው መግለጫ አመላክቷል።

በትናንትናው ዕለት ቡድኑ በድሬዳዋ ስታዲየም ከጅማ አባጅፋር ጋር ካካሄደው የ20ኛ ሳምንት ጨዋታ በኃላ ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለም መስፍን ከፍተኛ የስነ ምግባር ግድፈት ፈጽመዋል ሲል ገልጿል፡፡

አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ከዚህ ቀደም ቡድኑ በባህርዳር በነበረው ቆይታ  የስነ ምግባር ጉድለት ፈጽመው የነበረ ቢሆንም አጠቃላይ ለቡድኑ ውጤታማነትና አንድነት ሲባል በማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ተደርጎ እንደነበር አስታውቋል፡፡

የክለቡ ስራ አመራር ቦርድ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ተጫዋቾቹ በፈጸሟቸው የስነ ምግባር ግድፈቶች ዙሪያ የቡድን መሪው በተፈጸመው የሥነ ምግባር ጉድለት ዙሪያ በዝርዝር በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ቦርዱ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ለጊዜው ከቡድኑ ታግደው እንዲቆዩ ወስኗል፡፡

በመሆኑም አራቱ ተጫዋቾች ከድሬዳዋ በዛሬው እለት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርጓል ተብሏል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.