Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከ314 የግል አሰሪና ሰራተኛ ኤጀንሲዎች ባስመዘገቡት አድራሻ የተገኙት 150 ኤጀንሲዎች ብቻ መሆናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ መቀመጫቸውን ባደረጉ 314 የግል አሰሪና ሰራተኛ ኤጀንሲዎች ላይ ሲደረግ የነበረው ጥናት ይፋ ሆነ፡፡
ጥናቱ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ የኢትዮጵያ ሰራተኛና ማህበራዊ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካሳሁን ፎሎ እና የኢትዮጵያ አሰሪ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው ይፋ የሆነው፡፡
ጥናቱ ከሚመለከተው አካል ፍቃድን ሳያገኙ እየተበራከቱ የመጡና በዘርፉም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡ የመጡ የህግ ጥሰቶችንና ወንጀሎችን መነሻ በማድረግ የተካሄደ መሆኑ የተገለፁ ሲሆን በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ባደረጉ 314 የግል አሰሪና ሰራተኛ ኤጀንሲዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መካሄዱ ተነግሯል ።
በጥናቱ ወቅት ባስመዘገቡት አድራሻ የተገኙት 150 ኤጀንሲዎች ብቻ ሲሆኑ 71 የጥናት ቡድኑ ካስመዘገቡት አድራሻ ውጪ አፈላልጎ ያገኛቸው 28 የተዘጉ፣ 20 አድራሻ የቀየሩ፣ ዘጠኝ ምንም አይነት ቢሮ የሌላቸውና ቀሪዎቹ ቢሮ ለማሳየትም ፈቃደኛ ያልሆኑ ናቸው ተብሏል።
የጥናት ቡድኑ ባደረገው ምልከታም ከፌደራል ፖሊስ ብቻ የሙያ ፈቃድ ያላቸው 114፣ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ብቻ የስራ ፈቃድ ያላቸው 122፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ፈቃድ ብቻ ያላቸው 151 ኤጀንሲዎች ሲሆኑ በአሰራሩ መሰረት ከሶስቱም ተቋማት ህጋዊ የሆነ የሙያ የስራ እና የንግድ ፈቃድ ኖሯቸው የሚሰሩ ኤጀንሲዎች ግን 88 ብቻ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ከቢሮ አደረጃጀት አንፃርም 4 በመቶ ብቻ ተገቢው የቢሮ አደረጃጀት ኖሮት የሚሰራ ሲሆን፥ 34 በመቶ መካከለኛ እንዲሁም 62በመቶ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ መሆኑን አረጋግጧል ።
የሰራተኛ ምልመላ፣ የሰራተኛ ጥቅማ ጥቅም ማስከበር፣ የሰራተኛ ጉልበት ብዝበዛ ፣ የክፍያ አፈፃፀም እና የመሳሰሉ አሰራሮችም በጥናቱ በዝርዝር ትኩረት የተደረገባቸው ሲሆን መሟላት ያለባቸውን በአግባቡ አሟልተው እየሰሩ ያሉት ግን በጣም ጥቂቶቹ መሆናቸው ተነግሯል ።
ይህንን ጥናት መነሻ በማድረግም ውሳኔዎች የተላለፉ ሲሆን፥ በዚህም 144 ኤጀንሲዎች ፈቃዳቸውን መልሰው ከዘርፉ እንዲወጡ የተወሰ ሲሆን ከእንግዲህ በኋላ ግን በዘርፉ ተሰማርተው መስራት የሚፈልጉ ኤጀንሲዎች ከሶስቱ ተቋማት ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል ነው የተባለው፡፡
ውሳኔውም ከአንድ ወር በኋላ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል።
በትዝታ ደሳለኝ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.