Fana: At a Speed of Life!

በህንድ በአንድ ቀን ከፍተኛ የኮቪድ19 ተጠቂዎች ቁጥር ሲመዘገብ በሆስፒታሎች የኦክስጅን እጥረት ተከስቷል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በህንድ በአንድ ቀን ብቻ የተመዘገበው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ዓለም ላይ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በሃገሪቱ በ24 ሰአታት ውስጥ 346 ሺህ 786 ሰዎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው ይህም ኮቪድ19 ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ዓለም ላይ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ከዚህ ባለፈም 2 ሺህ 624 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋልም ነው የተባለው፡፡

አሁን ላይ በሃገሪቱ የቫይረሱን በከፍተኛ ፍጥነት መዛመት ተከትሎ ሆስፒታሎች የህክምና አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸውን ሬውተርስ በዘገባው አመላክቷል፡፡

በመዲናዋ ደልሂ በየአራት ደቂቃው በኮቪድ19 ሳቢያ አንድ ሞት እየተመዘገበ መሆኑንም ዘገባው ያመላክታል፡፡

ሆስፒታሎች የመተንፈሻ ኦክስጅን እጥረት እንዳጋጠማቸው ሲገልጹ፥ የታካሚ ቤተሰቦችም ኦክስጅን ለማግኘት የህክምና ባለሙያዎችን ሲማጸኑ ተስተውለዋልም ነው ያለው፡፡

ከዚህ ባለፈም ጃይፑር እና አምሪትሳር በተሰኙት ከተሞች ያሉ ሆስፒታሎችም የኦክስጅን እጥረት እንደገጠማቸው ተገልጿል፡፡

የሃገሪቱ መንግስትም ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ወደ ደልሂ ኦክስጅን በወታደራዊ አውሮፕላኖች እና ባቡር እያጓጓዘ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በህንድ 16 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች ኮሮና ቫይረስ ሲኖርባቸው እስካሁን 189 ሺህ 544 ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

ባለሙያዎች የሰዎች አኗኗር ጥግግት ለቫይረሱ መዛመት ዋናው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.