Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራሊዝም ስርአቱ የአተገባበር ችግር በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ላይ እንከን ፈጥሯል – የሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የነበረው የፌዴራሊዝም ስርዓት የአተገባበር ችግር በሃገሪቷ ትክክለኛ የዴሞክራሲ ስርአት እንዳይገነባ እንከን ሆኖ መቆየቱን የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።

የሰላም ሚኒስቴር ያዘጋጀው የፌዴራሊዝምና የሰላም ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት በአዳማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ፌዴራዝምና ለፌዴራሊዝም የስኬት ቁልፎች፣ የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የቋንቋ ብዝሃነት በዓለም አቀፋዊ ዕይታ፣ ፌዴራሊዝምና የውድድርና የትብብር ሥርዓቶች እና የግጭት አፈታት ሥርዓትን የሚዳስስ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት መከተል ከጀመረች ሶስት አስርት አመታት ብታስቆጥርም በትግበራ እና አፈፃፀም ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት እየተገነባ እንዳይሄድ እና በህገ- መንግስቱ የተደነገጉ መብቶች በአግባቡ ተፈፃሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዚህም ከህዝቡ የሚነሱ አዳዲስና ወቅታዊ ጥያቄዎችን በተገቢ መንገድ ለመመለስ የሚያስችል ብቃት እንዳይኖር አድርጓል ነው ያሉት።

በርካታው ህዝብም በፌዴራሊዝም ላይ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር በስርዓቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ማድረጉንም ዶክተር ስዩም ገልፀዋል።

የሰላም ሚኒስቴር በእነዚህ በተንከባለሉ ችግሮች ምክንያት ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመፍታትና ብዥታዎችን ለማጥራት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው የውይይት መድረክም የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት በጥናት ላይ የተመሰረተ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

ሚኒስቴሩ መድረኮችን በአውደ ጥናት፣ ስብሰባ፣ የፓናል ውይይትና ፎረሞችን በማዘጋጅት ተከታታይ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በመድረኩ በርካታ ምሁራን የተሳተፉበት ሲሆን “ፌዴራሊዝምና የሰላም ግንባታ በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.