Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳደሮች የተሳተፉበት የምስራቅና የደቡብ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች ከባቢያዊ የጎንዮሽ ግንኙነት የምክክር መድረክ እየተካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በፌዴሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅነት ርዕሰ መስተዳደሮች የተሳተፉበት የምስራቅና የደቡብ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች ከባቢያዊ የጎንዮሽ ግንኙነት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

መድረኩ የእርስ በእርስ ግንኙነት፣ ወንድማማችነት እህትማማችነት ሰላምና የጋራ ብልፅግናን ከማጠናከር አኳያ በቅርቡ የፀደቀው የመንግሥታቱ ግንኙነት አዋጅ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን የ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ ገልጸዋል፡፡

”መልካም ጉርብትና ለኢትዮጵያ ብልጽግና”  በሚል መሪ ሀሳብ የሰሜንና ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የምክክር መድረክ ከዚህ በፊት በባህርዳር ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

ከዚህ ጋር ተመሣሣይነት ያለው የምስራቅና የደቡብ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የእርስ በእርስ ምክክሮች፣ ስምምነቶችና ትብብሮች ማካሄድ ኢትዮጵያ ከምትከተለው ሕብረብሔራዊ  ፌዴራል ስርዓት ባህሪ የሚመነጭና ለስርዓቱ ጤናማነት፣ ውጤታማነትና ቀጣይነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ ትስስር በክልሎች መካከል ስለሚያስፈልግ ይህን ዓላማ ለማሳካት የተዘጋጀ  መድረክ መሆኑን አፈ ጉባዔው ገልጸዋል፡፡

የክልል መንግስታት የጋራ ጉዳዮችን በትብብርና በቅንጅት የሚሰሩበትን ሁኔታ ካልተፈጠረ የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ራዕይ የሆነውን አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ መገንባት እንደማይታሰብ አስታውሰዋል፡፡

በተጨማሪም የክልል መንግስታትን ግንኙነት ጤናማና ውጤታማ ካልሆነ በአገሪቱ ግጭቶችን በመከላከልና በመቆጣጠር ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ማረጋገጥ ስለማይቻል የመንግሥታትን ግንኘነት ጤናማ ማድረግ ልዩ ቦታ ይሰጠዋልም ሲሉ ነው ያስረዱት፡፡

በተጨማሪም የመንግስታት ግንኙነት ሥርዓትን ለመወሰን በቅርቡ የወጣው አዋጅ በፌዴራልና በክልል መንግስታት እንዲሁም በክልል መንግስታት መካከል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል ያሉ ሲሆን በአዋጁ መሰረት ተጎራባች ክልሎች እንደየአመቺነቱ የግንኙነት መድረኮችን በመፍጠር በሕዝቦች መካከል መቀራረብ፣ መተማመንን፣ የጋራ ብልፅግና፣ ዘላቂ ሰላምን፣ እኩልነት፣ አጋርነት፣ወንድማማችነትና መተባበር እንዲሰፍን በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል አፈ ጉባኤው።

በመጨረሻም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኘነት በሕግ መሠረት እንዲሆንና የህዝቦችን ሰላም እንዲጠበቅ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን በመድረኩ ላይ የኦሮሚያ፣ የደቡብ ፣ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የሐረሪ፣ የጋምቤላና የሲዳማ ክልል አመራሮች እየተሳተፉእንደሚገኙ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.