Fana: At a Speed of Life!

ለመጪዎቹ በዓላት ከ2 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚሰራጭ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለትንሳኤና ለኢድ አልፈጥር በዓላት ከ2 ሚሊየን ሊትር በላይ ፈሳሽ የምግብ ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሰራጨት መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በበኩሉ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪና የምርት እጥረት እንዳይኖር ኮሚቴ አዋቅሮ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ማህበር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አረጋ ማህበረሰቡ በቂ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችንና የእንስሳት ተዋፅዖዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ምርቶች እየገቡ ነው ብለዋል።

በመጋቢት ወር የገባ 63 ሺህ ኩንታል ጤፍ፣ 30 ሺህ ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ 1 ሺህ 800 ኩንታል ስንዴ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ እየተሸጠ መሆኑንም አብራርተዋል።

በአሥሩም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የህብረት ስራ ዩኒየኖች ከ80 ሺህ እስከ 800 ሺህ ሊትር ፈሳሽ የምግብ ዘይት ለበዓላቱ ወቅት ያስፈልግናል ባሉት መሰረት ግዥ በማከናወን ነጋዴዎች እያስገቡ መሆኑንም አቶ ሲሳይ ጠቁመዋል።

በዚህም 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ሊትር ፈሳሽ የምግብ ዘይት በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ለማህብረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚከፋፈል አስታውቀዋል።

በቂ የዳቦ ዱቄትና ስኳር አቅርቦት መኖሩን የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ማህበረሰቡ ከዚህ ቀደም በአንድ ወር 5 ኪሎ ግራም ይወስድ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት አሰራሩ በማሻሻል ሸማች በፍላጎቱ መሰረት ከ5 ኪሎ ግራም በላይ እንዲወስድ አቅጣጫ መቀመጡንም ነው የገለጹት።

የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አከበረኝ ውጋገን ለኢዜአ እንዳሉት በበዓላት ወቅት የዋጋ ጭማሪ ማድረግ፣ ባዕድ ነገር ቀላቅሎ መሸጥ፣ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ለገበያ በማቅረብ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚጥሩ ነጋዴዎች ይኖራሉ ሲሉም አሳስበዋል።

ወቅትና ሁኔታን እየጠበቁ በመሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ ያልተገባ ዋጋ ከመጨመር እስከ ምርት መሰወር የደረሱ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱንም ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች በኩል ምርቶችን በስፋት ማግኘት እንደሚችል በመግለጽ፤ ተገቢ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበርም ምክትል ኃላፊ ጠይቀዋል።

አቶ ሲሳይ አረጋ በበኩላቸው በከተማዋ የሚገኙ ሁሉም መሰረታዊ የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ቅዳሜን ጨምሮ ከመደበኛው ሰዓት ባለፈመ አገልግሎት እንዲሰጡ መወሰኑን በመግለጽ የምርት እጥረትና የአሰራር ክፍተት እንዳያጋጥም በጥንቃቄ ይሰራል ነው ያሉት።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.