Fana: At a Speed of Life!

ከ1 ሺህ 300 ሲ ሲ በታች በሆኑ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን ወደ 5 በመቶ እንዲቀንስ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ማሻሻያ በተደረገበት ረቂቅ የኤክሳይዝ ታክስ በአዳዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለውን የኤክሳይዝ ታክስ መጠን ከ30 በመቶ ወደ 5 በመቶ እንዲቀንስ ተደረገ።

የገንዘብ ሚኒስቴር በተሻሻለው የኤክሳይዝ ታክስ ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በተሻሻለው ረቂቅ ከ1 ሺህ 300 ሲሲ በታች ባሉ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን ከ30 በመቶ ወደ 5 በመቶ መውረዱን ገልጸዋል።

ይህም የተሽከርካሪዎችን ዋጋ እስከ 83 በመቶ ይቀንሰዋል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በሲጋራ እና አልኮል መጠጥ ላይ እንዲጣል የቀረበው ሃሳብ አነስተኛ ነው የሚል አስተያየት መቅረቡን ጠቅሰው፥ የመጠጥ ኢንዱስትሪው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲጋራ ላይ ብቻ ማስተካከያ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በዚህም በሲጋራ ላይ ተጥሎ የነበረው የ35 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ወደ 36 በመቶ ከፍ እንዲል በማሻሻያው መቅረቡን ጠቅሰዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው አያይዘውም በማሻሻያው በታሸጉ የውሃ ምርቶች ላይ ሊጣል የነበረው የ15 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ 10 በመቶ ሆኖ መቅረቡንም ነው የተናገሩት።

አምራቾች የውሃ ፕላስቲኮችን የመሰብሰብና አካባቢን እንዳይበክሉ የማድረግ ስራ እየሰራን ነው ማለታቸው ለማሻሻያው ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የቀረበውን ረቂቅ ማሻሻያ ተመልክቶ በቅርቡ ያጸድቀዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሚኒስትር ዲኤታው አንስተዋል።

ይህን መሰረት በማድረግ በመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ ታክስ የተጣለ በማስመሰል የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እስከመውሰድ የደረሰ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በሃብታሙ ተክለስላሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.