Fana: At a Speed of Life!

ፌዴራል ፖሊስ 600 የአድማ ብተና አመራሮችና ፀረ-ፈንጅ ሰልጣኞችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአዋሽ 7 ማሰልጠኛ ሲያሰለጥናቸው የነበሩ 600 የመጀመሪያ ዙር ከፍተኛና መካከለኛ የአድማ ብተና አመራሮችና መሰረታዊ የ4ኛ ዙር የፀረ-ፈንጅ ሰልጣኞችን አስመረቀ።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ በመገኘት ለተመራቂዎቹ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴርና የክልል የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በከፍተኛ መስዋእትነት እየሰራ ባለበት ወቅት ለምረቃ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

በተቋሙ እየተካሄዱ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን መሰረት በማድረግ የሰራዊቱን ህይወት ለማሻሻልና ሰራዊቱ ከተቋሙ በጡረታ በክብር  ሲሰናበት የማያርፍበትና ሰርቶ የሚኖርበት የፖሊስ ፋውንዴሺን የማቋቋም ስራ ተጀምሯል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ለሀገሩ ሰንደቅ ዓላማና ክብር ሲል ከገንዘብ በላይ የሆነውን ውድ ህይወቱን መስዋእት እያደረገ ያለውን ሰራዊት ጥያቄዎች ለመመለስ ሁሉም የተቋሙ አመራሮች ጊዜያችንን በሙሉ በመስጠት እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡

ቀጣዩ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ፖሊስ ከማንኛውም የፖለትካ ፓርቲ ገለልተኛ በመሆን ለሁሉም የፖለትካ ፓርቲዎች ሰላምና ጸጥታን የማስከበር አገልግሎቱን በመስጠት ህብረተሰቡ የሚፈልገውን መርጦ ወደ ስልጣን እንዲያመጣ የሚጠበቀውን መወጣት ይገባል ነው ያሉት።

እስካሁንም ባለው ሂደት የምርጫ ጣቢያዎችን በመጠበቅና መራጩ ህብረተሰብ ያለምንም ተፅእኖ እንዲመዘገብ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በተባበር እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሀገሪቱ በአራቱም ማዕዘን የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ፀረ-ሰላም ሀይሎችን በመደምሰስ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የበለጠ መስራት እንደሚገባ ኮሚሽነር ጄነራሉ አሳስበዋል፡፡

ተመራቂዎቹ በማሰልጠኛ ቆይታቸው የፖሊስ ባህልና ጨዋነት፣ በተቋሙ የለውጥ ስራዎች፣መሪነትና የመሪነት ሚና፣ሰብዓዊ መብትና የፖሊስ እርምጃ አወሳሰድ፣በምርጫ ሂደት የፖሊስ ሚና፣የፀረ-ሽብር ትምህርት፣የአድማ ብተና፣የኮምፓስ፣የካርታ ንባብና የ‘ጂፒኤስ’ (GPS)፣የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር፣የፀረ-ፈንጅ፣የመጀመሪያ የሂክምና እርዳታ ትምህርቶችን የወሰዱ ሲሆን በመስክ የተለያዩ የአካል ብቃት ስልጠናዎች መውሰዳቸውን በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ የሰው ሀብት ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተርና የትምህርትና ስልጠና ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ሰማሀኝ ይደነቅ መግለፃቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአድማ ብተና አመራሮቹ በጽንሰ ሐሳብ ከተማሩት በተጨማሪ ተግባር ተኮር የሆኑ የአድማ ብተና ስልጠናዎችን በከፍተኛ የውድድር መንፈስ ማጠናቀቃቸውን ምክትል ኮማንደር ሰማህኝ ይደነቅ አብራርተዋል፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.