Fana: At a Speed of Life!

በበርሊንና ፍራንክፈርት ሚሲዮኖች አስተባባሪነት ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከ41 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በበርሊንና ፍራንክፈርት ሚሲዮኖች አስተባባሪነት ለሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች ከ41 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በጀርመን በርሊንና ፍራንክፈርት እንዲሁም በቼክ ሪፐብሊክ፣ ፖላንድ፣ ዩክሬንና ስሎቫክ ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ጋር ባደረገው ውይይት በርሊንና ፍራንክፈርት ሚሲዮኖች አስተባባሪነት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ41 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተሰብስቧል ብሏል፡፡
ድጋፉ ለህዳሴ ግድብ፣ ለኮቪድ-19 መከላከል፣ ለገበታ ለሃገር፣ ለመከላከያ ሰራዊትና ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት አመታት በርካታ ሀገራዊና ዲፕሎማሲያዊ እድሎችና ፈተናዎችን ማለፏን ገልፀው በሂደቱ ዳያስፖራው ስለነበረው ገንቢ አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተማረ የሰው ሃይል በከፍተኛ ደረጃ የሚፈልስባት ሀገር በመሆኗ ምሁራን የዳያስፖራ አባላቱ በዕውቀት ሽግግር ላይ ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ቆንስል ጀነራል አቶ ፈቃዱ በየነ በበኩላቸው የኤጀንሲው ተቋማዊ አቅም እየተጠናከረ መምጣቱ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንስተው ፅህፈትቤቱም ዳያስፖራውን ለማስተባበር ከምን ጊዜውም በላይ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በጀርመን የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙሉ ሰሎሞን ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያን ከእንግዲህ ወደኋላ የሚመልሳት እንደማይኖር፣ መንግሥትና ህዝብም በጋራ በመቆም አንድነታቸውን ጠብቀው የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንደሚሻገሩ አውስተዋል፡፡
አያይዘውም ዳያስፖራው የጀመረውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.