Fana: At a Speed of Life!

በአጣዬና ጭልጋ አካባቢ የተፈጸመውን የወንጀል ድርጊት የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ወደ ስፍራው ተላከ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአጣዬና ጭልጋ አካባቢ በሰብአዊና ቁሳዊ ሃብት የተፈጸመውን የወንጀል ድርጊት የሚያጣራ የምርመራ ቡድኖች ወደ ስፍራው መላካቸውን የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

ዐቃቤ ሕጉ አቶ ገረመው ገብረጻዲቅ እንደገለጹት፤ የተላከው ቡድን ከፌዴራልና ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ፖሊስ የተውጣጡ አባላት ይዟል።

በአጣዬና አካባቢው በሰው ህይወት መጥፋት፣ በአካል መጉደል፣ በንብረት መውደምና በሰዎች መፈናቀል የደረሰው ጥፋት ተራ ግጭት ሳይሆን ለዘመናት የተገነባ ከተማን ያወደመ አስከፊ የወንጀል ድርጊት መሆኑን አመልክተዋል።

የወንጀል ድርጊቱን በልዩ ትኩረት ለማጣራት የፌዴራልና የክልሉ ተቋማት የጋራ የምርመራ ቡድን በማቋቋምና እቅድ በማውጣትና አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ሃብት ውድመት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ የማቅረብ ስራ እንደሚከናወን ያመለከቱት ዐቃቤ ሕጉ፤ የምርመራ ቡድኑ ባጭር ጊዜ ውስጥ ስራውን ከማጠናቀቅ ባሻገር በማጣራት ሂደቱ የሚገኘውን ውጤት በተከታታይ ለህዝቡ የሚገልጽ መሆኑን ጠቁመዋል።

የታክቲክና የቴክኒክ ስልቶችን ተጠቅሞ በሚከናወነው ምርመራ የአካባቢው ማህበረሰብ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት፣ ማስረጃ በማቅረብና ምስክር በመሆን እንዲተባበር ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ በማዕከላዊ ጎንደር ጭልጋ አካባቢ ከቅማንት ማንነት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚፈጸመውን የወንጀል ድርጊት የሚያጣራ መርማሪ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን ተናግረዋል።

በክልሉ በየትኛውም አካባቢ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ማስቆም የሚቻለው በየደረጃው የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ሲቻል መሆኑን ህብረተሰቡ በመገንዘብ ተባባሪ እንዲሆን መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የህዝቦችን ደህንነት ለመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ነው ያረጋገጡት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.