Fana: At a Speed of Life!

በመቐለ ከተማ ማዕከል በማቋቋም እርዳታ በቅርበት ለወረዳዎች እንዲዳረስ እየተደረገ  ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ )በአሁኑ ወቅት በመቐለ ከተማ ማዕከል በማቋቋም ማንኛውም እርዳታ በቅርበት ለወረዳዎች እንዲዳረስ እየተደረገ  መሆኑ ተገለጸ።

ቻታም ሀውስ የተባለው የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ለንደን  ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የበይነ መረብ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ወሳኝ እና ዓለም አቀፋዊ የሆኑ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ስራ አስፈጻሚዎች፣ የሰብአዊ መብት ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በብሪታንያ መንግስት አፍሪካ ተኮር የልማት ድርጅት ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ፣ ዓለም አቀፍ የግጭትና ቀውስ ትንተና ባለሙያዎች እና አፍሪካ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ተቋማትን ጨምሮ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ÷  በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር እርምጃው መጠናቀቅን ተከትሎ በመጀመሪያ ዙር ለ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች መደረጋቸውን፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች ተመሳሳይ ድጋፍ መቀጠሉን ገልፀዋል።

ለሰብዓዊ ድጋፍ መንግስት ከ3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማውጣቱን ተናግረዋል፡፡

ከተደረገው ድጋፍ ውስጥ 70 ከመቶው ከመንግስት 30 በመቶው በአለም አቀፍ ድርጅቶች የተሸፈነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም እርዳታ ሰጪዎችም ሆነ መገናኛ ብዙሃን ለሰላም ሚኒሰቴር በማሳወቅ ብቻ ወደክልሉ መግባት ይችላሉ ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት በመቐለ ከተማ ማዕከል በማቋቋም ማንኛውም እርዳታ በቅርበት ለወረዳዎች እንዲዳረስ እየተደረገ መሆኑን ያመለከቱት ኮሚሽነር ምትኩ ÷በጤና ሚኒስቴር በእርዳታ የተሰጡ የህክምና መሳሪያዎች፣ መድሃኒቶች እና አምቡላንሶች ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በየወረዳው የተንቀሳቀሽ ህክምና ማዕከል አቋቁመው አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስትና ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች በገቡት የማስተባበርና የሰብአዊ  እርዳታን የማቅረብ ውል መሰረት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባቸው ከ5 አመት በታች ለሆኑ ህፃናት እና ለነፍሰ ጡር ሴቶች የሚደረገው የአልሚ ምግብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀርብ ለእርዳታ ሰጪዎች ጥሪ አቅርበዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ለህጻናት ከ1 ሚሊየን በላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያዎችን ማቅረቡን የገለፁት ኮሚሽነር ምትኩ መጪው ጊዜ የዝናብና የእርሻ ወቅት በመሆኑ ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የግብርና ግብአቶች ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት

ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ የሆኑት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቋሚ ተጠሪና የሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ ካትሪን ቦሴ በበኩላቸው÷ ያጋጠሙት ችግሮች ፈታኝ ቢሆኑም ከመንግስት ጋር ተባብሮ በመስራት ፈተናዎቹን ማለፍ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የድንበር የለሽ ሃኪሞች ዳይሬክተር ጀነራል ኦሊቨር በህን ችግሮች ቢኖሩም መንግስት ለዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ወደ ክልሉ በፈለጉት ጊዜ እንዲገቡ የፈቀደ መሆኑ ሊመሰገን እንደሚገባው ተናግረው፣ የእርዳታ አቅርቦቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.