Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያን አገለግላለሁ የሚል እኩል መብት የሚያገኝበት ምርጫ እንዲሆን እንፈልጋለን – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያን አገለግላለሁ የሚል እኩል መብት የሚያገኝበት ምርጫ እንዲሆን እንፈልጋለን አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገጻቸው ላይ እንደገለጹት እያንዳንዱ ዜጋ ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን አውቆዛሬ ጀምሮ ማንን ለምን እንደሚመርጥ እያሰበ እንዲቆይ አሳስበዋል፡፡

ምርጫውን ተከትሎም ድንጋይ የሚወረወር ካለ ሕብረተሰቡ በጋራመቆም መከላከል እንዳለበት ነው ያስታወቁት፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥም ከምርጫ በስተቀር የሚሸጋገር፣ የሚደራደር መንግሥት አይፈጠርም ብለዋል።

ማንም ሰው ሥልጣን መያዝ የሚችለው በምርጫ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ዐውቆ የሚፎካከር ኃይል ሐሳብ ካለው፣ አደረጃጀት ካለው፣ ሐሳቡን ሽጦ፣ ሕዝብ አሳምኖ እንዲመረጥ ጥረት ማድረግ አንደሚኖርበት ነው የገለጹት፡፡

በተጨማሪም ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የምንፈልግ ኃይሎች በተቻለ መጠን አውዱ ለዚያ የሚመች መሆኑን ዐውቀን በመሥራት ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ የሥልጣን ሽግግር እና ቅቡል መንግሥት መፍጠር ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል።

ከዚህ ውጪ ያሉ ሐሳቦች ሁሉ ቅዠቶች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይሆኑም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመርነውን የዲሞክራሲ ጉዞ ያደናቅፉ ይሆናል እንጂ አይሳኩም፡ ዲሞክራሲ አብቦ እንዲያፈራ፣ ተፎካካሪዎችም፣ ሕዝብም፣ መንግሥትም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።

ኢትዮጵያን አሽናፊ የሚያደርገው ምርጫ ሰላማዊ፣ ሁሉም የሚፎካከሩ ኃይሎች እኩል መድረክ የፈጠረ፣ በሐሳብ የላቀ፣ በተግባር የበቃ፣ በልምድ የተካነ፣ ቃል ከመግባት ሳይሆን ሠርቶ ለማሳየት የቆረጠ፣ሕዝቡን የሚያደምጥ፣ ሕዝቡን የሚያከብር፣ የማይሰርቅ፣ ኃይል ሥልጣን የሚይዝበት ምርጫ እንዲሆን እንፈልጋለን ነው ያሉት።

በዚህ ምርጫ ያሻችሁን ምረጡ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ሰላምን አስቀድሙ፣ በዚህ ምርጫ ያሻችሁን ምረጡ፤ ግን እኩል መድረከ መፈጠሩን አረጋግጡ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲገባ የማይፈለግ ኃይል መኖር የለበትም፤ ለኢትዮጵያ የቀና፣ኢትዮጵያን አገለግላለሁ የሚል እኩል መብት የሚያገኝበት ምርጫ እንዲሆን ከልባችን እንፈልጋለን፤ ይህ ሲሆን ብቻ ነው ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆነው ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.