Fana: At a Speed of Life!

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአምስት ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በኪንፋዝ በገላ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የኪንፋዝ በገላ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ተስፋዬ ጥሩነህ ለአሚኮ እንዳሉት÷ ከኪንፋዝ በገላ ወረዳ ስላሬ ከተማ ወደ አምባ ጊዮርጊስ ሲሄድ የነበረ ተሸከርካሪ ተገልብጦ የሰው ሕይወት አልፏል፡፡

በወረዳው ጭቅቂ ቀበሌ በተለምዶ መሳለሚያ በተባለ ስፍራ በደረሰ የትራፊክ አደጋ ነው የሰው ሕይወት የጠፋው፡፡

በደረሰው አደጋ የምስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በ6 ሰዎች ከባድ ጉዳትና በአምስት ሰዎች ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት፡፡

አደጋው የደረሰው ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ ሲሆን÷ አደጋውን ያደረሰው የጭነት አይሱዚ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ለበዓል የሚሄዱ ሰዎችን ይዞ ሲጓዝ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ተሽከርካሪው ዳገት ሲወጣ ወደ ኋላ በመንሸራተቱ በግምት 40 ሜትር የሚሆን ገደል ውስጥ መግባቱንም ተናግረዋል፡፡

የመንገዱ አለመመቸት ለአደጋው እንደመንስኤ እንደሚጠቀስ የገለፁት ዋና ኢንስፔክተሩ÷ በቂ የሆነ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ተጓዦቹ በጭነት አይሱዚ ለመጓዝ መገደዳቸውን ነው የተናገሩት፡፡

አሽከርካሪው መኪናውን ጥሎ መሰወሩንና ፖሊስ ክትትል እያደረገበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ማኅበረሰቡ የሕዝብ ተሽከርካሪን ተመራጭ በማድረግ ራሱን ከአደጋ እንዲከላከልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትራንስፖርት ችግር ሲፈጠርም ከወረዳው የአስተዳደር ምክር ቤት ጋር እየተነጋገረ ችግሩን መፍታት እንደሚገባም መናገራቸውን አሚኮ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.