Fana: At a Speed of Life!

ከብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፥

የሀገራችን ችግሮች ተናጥላዊ አይደሉም። ውስብስብና የተሣሠሩ ናቸው፡፡ ፖለቲካው ከኢኮኖሚው፣ ዲፕሎማሲው ከማኅበራዊ ጉዳዮቻችን ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው፡፡ ሀገራችን ቀደም ባሉት ጊዜያት ተከታታይ ዕድገቶችን ማስመዝገብ ብትችልም ዕድገቱ የመጣበት መንገድ ጤና ባለመሆኑ የዕድገት ጥራት ጉድለት ዋነኛው ችግራችን ሆኖ ቆይቷል። በዚህ የተነሣ የኢኮኖሚያችን ምርታማነት በጣም ዝቅተኛ ነው! ዜጎች ከዕድገቱ በቂ ጥቅም ሊያገኙበት ቀርቶ የፈሰሰበትን መዋዕለ ንዋይ በበቂ አልመለሰም።

በአኃዝ የተጠቀሰው ዕድገትም በብድር ጫና ምከንያት ራሱን ማስቀጠል አልቻለም፡፡ ለውጡን ተከትሎ በወሰድነው ርምጃ ኢኮኖሚው ዜጎችን በፍትሐዊነት ተጠቃሚ እንዲያደርግ፣ ዕድገቱ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጎጆ ውስጥ አንዲገባ፣ በብልሹ አሠራርና በዘፈቀደ የባከነው የሀገራችን ሀብት በጥብቅ ቁጥጥርና የፕሮጀከት አፈጻጸም ዲሲፕሊን እንዲመራ፣ በዕዳ ጫና ተንገራግጮ የቆመው ኢኮኖሚ ከገባበት ማጥ ተመንጥቆ እንዲወጣ፣ የተራገፈው የሀገራችን ካዝና እንዲሞላ ግልጽ ግቦችን አስቀምጠን፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ቀርጸን ተንቀሳቅሰናል።

አሁን በዕዳ ጫና ጎብጣ የነበረች ሀገራችን በመጠኑ ቀና ብላለች፡፡ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲቆም የደረሰው ኢኮኖሚያችን ሞተሩ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ በስግብግብነት ሰፊ የሀገር ሀብት እየተመዘበረባቸው በአደባባይ ምንም ሳይሠሩ ሸረሪት ያደራባቸው ፕሮጀከቶች ነፍስ ዘርተው ወደ ፍጻሜ እየደረሱ ነው። ተኮላሽተው የነበሩ እንደ ሕዳሴ ግድብ እና ስኳር ፋብሪካዎች የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀከቶቻችን በጥብቅ ግምገማና ዲስፕሊን ግንባታቸው ተቀላጥፏል። ተንገራግጮ የቆመው ኢኮኖሚያችን እጅግ አስቸጋሪ የነበረውን ጊዜ አልፎ፣ በዘርፉ መሪዎች ጥንቃቄና በዜጎች ትብብር ወደ ጎዳናው ማስገባት ችለናል።

በተለይም ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በተመደበው ጊዜና ሀብት የማጠናቀቅ ልምድ በሀገራችን እንዲፈጠር፣ ያቀዱትን የማሳካት ጉዳይ ተቋማዊም ሀገራዊም የባህል መሠረት እንዲኖረው ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። ኢትዮጵያ ሐሳብ የሚወጠንባት ብቻ ሳትሆን የሚተገበርባት፣ ሥራዎች ተጀምረው የሚጠናቀቁባት ሀገር እየሆነች መምጣቷን እያየን ነው።

የተበላሸውን ማረም፥ የተደፋውን ማቃናት ብቻውን ሀገራችንን ከኋላቀርነት ሊያላቅቃትና ወደ ብልጽግና ማማ ሊያደርሳት አይችልም፡፡ ቀና ብሎ ትልቁን ሕልም አይቶ፣ በሩቁ አልሞ፣ ረጅሙን ተራራ ለመውጣት ድፍረትና ወኔ፥ ቁርጠኝነትና ጽናት ይጠይቃል። ይህም የተደፋውን ከማቃናትና፣ የተበላሸውን ከማረም ይጀምራል። ከዚያም ወደ ነገ የሚያሻግረንን፣ ለልጆቻችን የበለጸገችና የሚኮሩባት ኢትዮጵያን የሚያስረከብልንን የብልጽግና ዕቅድ ማለም ይገባናል። ሕልሞች ሩቅ በመሆናቸው እስከንደርስ ድረስ ለቅርብ ተመልካቾች አይታዩም፡፡ ግቦቻችን ውስብስብ ስለሆኑ ቀላሱን ለሚያሳድዱ ወንድሞቻችን በቀላሉ አይረጋገጡም።

የቱሪዝም ሴከተሩ መነቃቃት አንዳለበትና ሀገራችን ያላትን በቱሪዝም የመልማት ዕምቅ ዐቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ሴክተሩ እስከዛሬ ውል በሌለው ገመድ ተተብትቦ አመርቂ ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሀገራችን ብዙዎች በምኞት የሚጎበፎትና በቱሪዝም ዘርፍ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ለማድረግ ዘርፉን የሚያነቃቁ በርካታ ፕሮጀከቶች ተሠርተዋል፤ ሊሆኑ አይችሉም የተባሉ ሕልሞች እውን መሆን ጀምረዋል። በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገራችን ከፍሎች ተግባራዊ በመሆን ላይ ናቸው

የሀገራችንን ኋላ ቀር የግብርና ምርት ሂደት መቀየርና እስከዛሬ ያልተጠቀምንባቸውን መሬቶች ወደ ምርት ሂደት ማስገባት የኢኮኖሚ ማሻሸያ አንዱ ግባችን ነበር፡፡ በዝናብ ላይ ጥገኛ ከሆነውና በዓመት አንዴ በማምረት ብዙ መሬትና ዐቅም ከሚያባከነው ዘልማዳዊ አሠራራችን ተላቅቀን ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ የምትገዛበትን ሁኔታ ለመቀየር ቆርጠን ሠርተናል፡፡
በዚህም መሠረት ከ145ሺህ ሄከታር በላይ መሬቶችን በስንዴ በማልማት ሕልማችን ከግቡ እንደሚደርስ በአጭር ጊዜ ውስጥ አረጋግጠናል። ዘርፉ የተተበተበበትን የግብዓት አቅርቦት በመፍታት፣ ዘመናዊ የእርሻ ቴከኖሎጂዎችን በማቅረብ፣ እርጥበትን በአግባቡ በመጠቀም እና በኩታ ገጠም በማምረት ግብርናን ለማዘመን የያዝነው ዕቅድ ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ጀምሯል።

ውድ ኢትዮጵያውያን፥

ከለውጡ ማግሥት ከገጠሙን ፈተናዎች መካከል እነዚህ ሦስቱ ይጠቀሳሉ፡፡ የዓለምን ኢኮኖሚ ያንኮታኮተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በሀገራችንና በቀጣናው ተከሥቶ ከፍተኛ እህል ያወደመው የአንበጣ መንጋ፣ በሕግ አልገዛም ያሉ አብሪተኞች በሁሉም አቅጣጫ የከፍቱት ጦርነት፡፡ ሌሎችም ፈተናዎች ነበሩ። ሆኖም የኮቪድ አደጋንም ሆነ ሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ለመቋቋም በጥንቃቄና በተጠና መንገድ ኢኮኖሚያዊ ርምጃዎችን ለመውሰድ ችለናል፡፡ በዚህም ምክንያት ፈተናዎችን መቋቋም ብቻ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ማነቆ የነበሩብንን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት መቻላችንን የሚያረጋግጡ በርካታ ድሎች አስመዝግበናል።

ለአብነት ያከልም፣ እጅግ አነስተኛ የሆነው የሀገር ውስጥ ቁጠባ አድጓል። በዚህም በተደጋጋሚ ዓመታት በጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲፈተን የነበረውን የኢኮኖሚ ችግር እየቀረፍን መጥተናል። ይህም ከፍተኛ ብድርን ለግሉ ዘርፍ ማቅረብ አንድንችል አድርጎናል። የወጪ ንግድ በተከታታይ ዓመታት ከነበረበት የቁልቁለት ጉዞ በመውጣት ከአምና ጀምሮ ወደ ተከታታይ ዓመታት እድገት ገብቷል፡፡ ዘንድሮ የ21 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ለመጀመሪያ ጊዜ አሥረኛው ወር ላይ ሳይደረስ የወጪ ንግድ ገቢ ከ2 ቢሊየን ዶላር ሊሻገር ችሏል። ይህም ካለፈው ዓመት የ10 ወራት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የ17 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራ ከግል ሴክተር መነቃቃት ጋር እንዲሁም የቆሙ ፕሮጀከቶች ወደ ሥራ ከመግባታቸው ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ዕድገትን እያስመዘገበ ይገኛል።

የኢኮኖሚው ችግሮችን ለማረም ባደረግነው ከፍተኛ ጥረት አብዛኛው የዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ከዜሮ በታች በሆነበት ጊዜ፣ የሀገራችን ኢኮኖሚ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን በመቋቋም አዎንታዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ችሏል። ያም ሆኖ፣ የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች በኢኮኖሚው ላይ ጫና ሳይፈጥርበት አልፏል ማለት አይቻልም፡፡ በተለያዩ የመፍትሔ አማራጮች ተጽዕኖችን ለማጥፋት ቢሞከርም ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ግን አልተቻለም።

ከተጽዕኖዖቹ አንዱ የዋጋ ንረት ነው፡፡ የዋጋ ንረት ለረጅም ጊዜ የሀገራችን ኢኮኖሚ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ የገጠሙንንን ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ፈተናዎችን ተቋቁመን፣ የኑሮ ውድነት ሕዝባችንን አደጋ ላይ እንዳይጥለው ለማድረግ፣ ፈተናዎቹ ከተከሠቱባቸው ቀናት ጀምሮ አስፈላጊዎቹን ርምጃዎች ሁሉ ስንወስድ ነበር፡፡ ሆኖም ችግሩ ከሀገራዊና ከዓለም አቀፍ ችግሮች ጋር የተገናኘ በመሆኑ ችግሩን ተቆጣጥረን ለመቆየት ያደረግነው ጥረት የምንፈልገውን ያክል ውጤታማ ሆኖ አልተገኘም። ይህም በሕዝባችን ኑሮ ላይ የፈጠረውን እክልና አደጋ በመረዳት የኑሮ ውድነቱን ሊቀርፉ የሚችሉ ርምጃዎችን በተጠና መንገድ መውስድ ጀምረናል።

የግል ባለ ሀብቱ መሠረታዊ ሸቀጦችን በቀላሉ ወደ ሀገር አንዲያስገባ የሚያስችሉ አሠራሮችን በመዘርጋት በአጭር ጊዜ ውስጥ የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር እየተንቀሳቀስን እንገኛለን። መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የወሰዳቸውና እየወሰዳቸው ያሉ ርምጃዎች ኢኮኖሚውን ከነበረበት ችግር ውስጥ አውጥተው ወደ ፊት የሚያስፈነጥሩና የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

ሆኖም ሀገራችን ከውጭም ከውስጥም በጠላቶች በተወጠረችበት በዚህ ጊዜ ችግሮቻችንን ለመፍታት በአንድ ላይ መቆምና መተባበር እንደሚያስፈልገን ነጋሪ አያሻውም! በምንወስዳቸው ርምጃዎችና የኢኮኖሚውን ፈተናዎች ለመቅረፍ በምናደርገው ጥረት ሁሉ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከጎናችን አንዲቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን።

መዳረሻችንን የሚያሳየን መነሻችን ነው፡፡ በመነሻችን ያስመዘገብናቸውን ስኬቶች አጎልብተን ለብልጽግና እንደምንበቃ፣ ሀገራችንንም ከፍ ካሉት ተርታ እንደምናሰልፋት ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።

በዓለም ላይ ያለው ጨለማ ሁሉ የአንዲት ሻማን ብርሃን ሊያጠፋ አይቻለውም፡፡ የፈተናዎች ብዛትም የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ አያስቆመውም። የቤታችን ጉዳይ የቤታችን ብቻ ነው። በር ዘግተን፣ ማዕድ ከበን እንፈታዋለን፡፡ የቤታችን ጉዳይ አደባባይ ላይ አስጥተን ለጠላት መምቻ፣ ለጎረቤት መተረቻ፣ የምናቀብል ሞኞች አንሆንም። የኢትዮጵያን ጥንካሬና ልዕልና ላለማየት የተሳሉ ብዙዎች የቻሉትን ጫና ሁሉ እየጎረፉት ነው፡፡ በአንድነት ጸንተን፣ እያራገፍነው አንደምንሄድ በዚሁ አጋጣሚ ልንነግራቸው እንወዳለን።

የብሔራዊ ማከሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.