Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር መለስ ዓለም ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቼል ኦማሞ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኬንያ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ከኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቼል ኦማሞ ጋር ተወያዩ።

በውይይቱ ወቅት አምባሳደር መለስ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ ዶክተር አርከበ እቁባይ ለተባበሩት መንግስታ ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት በእጩነት መቅረብን እንዲሁም የቀጣዩ ብሔራዊ ምርጫን በተመለከተ ለሚኒስትሯ ገለፃ አድርገዋል።

የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቼል ኦማሞ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህ መሰረት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ሆነ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እልባት እንደሚያገኝ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

በአጎራባች ሃገራት መካከል ድንበሮች የትብብር እንጅ የግጭት ምንጭ መሆን እንደሌለባቸው በመግለጽም ኢትዮጵያ ቀጣዩን ብሔራዊ ምርጫ በስኬት እንደምትወጣ እምነቱ አለኝ ብለዋል።

በሌላ በኩል ዶክተር አርከበ እቁባይ ለተባበሩት መንግስታ ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት በእጩነት መቅረብ በአፍሪካ ህብረት በኩል ድጋፍ የተሰጠው መሆኑን ገልፀው፣ ኬንያም ድጋፏን እንደምትሰጥ አረጋግጠዋል።

ኬንያ በሁለቱ ሃገራት ያለው ረጅም ዘመናት ያስቀጠረውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግና ለዚህም በሃገራቱ መካከል የተፈረሙ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

አምባሳደር መለስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መርህ ፅኑ አቋም ያላት መሆኑን ጠቅሰው፥ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ሆነ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ በዚህ አግባብ መፍትሔ ማግኘት እንደሚችል ጠቅሰዋል።

ናይል የሁሉም የተፋሰሱ ሃገራት መሆኑን በማንሳት ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል ስርዓት መስፈን እንዳለበት ኢትዮጵያም የታችኞቹ የተፋሰሱ ሃገራት በዚህ መሰረት መጠቀም ይገባቸዋዋል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ጉዳይን በተመለከተም ሃገራቱ ድንበር ብቻ ሳይሆን ህዝቦችንም የሚጋሩ በመሆናቸው ድንበራቸው የግጭት ሳይሆን የትብብር አካል መሆን እንዳለበት በማንሳት፥ ሱዳን በወረራ የያዘችውን የኢትዮጵያ ግዛት ስትለቅ በሰላማዊ መንገድ በድርድር መፍታት ይቻላል ነው ያሉት፡፡

ቀጣዩ ብሔራዊ ምርጫ መጪውን የኢትዮጵያን እድል የተሻለ ከማድረግ አንጻር ጉልህ አስተዋጾኦ ያለው በመሆኑ ነፃ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ እንዲሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.