Fana: At a Speed of Life!

በእየሩሳሌም ከተማ በጎሎጎታ የትንሳዔ በዓል በድምቀት ተከብሯል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በእየሩሳሌም ከተማ በጎሎጎታ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ሥልጣን መድኃኔዓለም ገዳም የትንሳዔ በዓል በድምቀት ተከብሯል፡፡

በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፣ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ረታ ዓለሙ፣ አባቶች መነኮስት ካህናት፣ መዘምራን፣ ምዕመናን በተገኙበት ነው የተከበረው፡፡

በበዓሉ ላይ የእስራኤል ምክትል ሚንስትር ጋዲ ይባርክን በቦታው ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ በማለት በሰጡት ቃለ ምዕዳን በዓሉ በሰላምና በመንፈሳዊ ደስታ እንዲከበር አባታዊ ቡራኬ ሰጥተው፣ እግዚአብሔር አምላክ በዚች ዕለት የማዳን ሥራውን የፈፀመባት ዕለት ናት ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም “ዛሬ ክብርና ፀጋ ያገኘንበት፤ ጠፍተን የነበርነው የተሰበሰብንበት ዕለት ነው” በዚህ እለት ሕሊናችን ሊያስበው የሚገባው ምን ዓይነት ድህነት ነው፣ ምን አይነት ፍቅር ነው የሚለው ነው፤ ሞትን ይሽረው ዘንድ፣ ሙታንን ያስነሳቸው ዘንድ፣ የማይሞተው ሞተ” ሲሉ ለምዕመናኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

“ሕያውን ስለምን ከሙታን መካከል ትፈልጉታላችሁ? እሱ ሞቶ የሚቀር አምላክ አይደለም። በራሱ ፈቃድ ሞተ፣ ስለሰው ፍቅር ብሎ ሞተ። በሦስተኛው ቀን በልዩ ሥልጣን፣ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ” ብለዋል ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም፡፡

ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ለአቶ ጋዲ በበዓሉ በመገኘታቸውና እያደረጉት ለሚገኙት ትብብር በእግዚአብሔር ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አምባሳደር ረታም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በተመሳሳይ ለአቶ ጋዲ ምስጋና ማቅረባቸውን ከእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.