Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ከልክ በላይ በሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ከ1 ሺህ 500 እስከ 500 ብር የሚያስቀጣ አዲስ መመሪያ ወጣ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከዛሬ ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆን ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ከልክ በላይ በሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ከ1 ሺህ 500 እስከ 500 ብር የሚያስቀጣ አዲስ መመሪያ ማውጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ያልሆኑ ተሽከርካሪዎች የተሳፋሪ ቁጥር ወይም የመጫን አቅም በተሽከርካሪው ወንበር ልክ መሆኑ ኢንጂነር ስጦታው አካለ ገልጸዋል፡፡

በዚሁም መሰረት የሚኒባስ ታክሲ የመጫን አቅም በተሽከርካሪው ወንበር ልክ ሲሆን፥ ከኋላ ወንበር 3 ሰው ብቻ እንዲጭኑ ተወስኗል፡፡

የሀይገር እና ቅጥቅጥ አውቶቡስ ደግሞ የመጫን አቅም በተሽከርካሪው ወንበር ልክ እና በተጨማሪ 5 ሰው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ፣ የሸገር የብዙኀን ትራንስፖርት እና የመንግስት ሰራተኞች ሰርቪስ አውቶቡሶች የተፈቀደ የትራንስፖርት ተሳፋሪ ቁጥር ወይም የመጫን አቅም በተሽከርካሪ ወንበር ልክ እና በቁም ለመጫን ከተፈቀደው 50 በመቶ ሰው መሆኑም አስታውቀዋል፡፡

ማንኛውም ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) የጭነት ልክ አሽከርካሪውን ጨምሮ ሦስት ሰው ሲሆን ባለ አራት እግር (ባጃጅ) ተሽከርካሪ የመጫን አቅም በወንበር ልክ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ታክሲ እና ሌሎች መሰል የሜትር ታክሲ ተሽከርካሪዎች ደግሞ  የተሳፋሪ የጭነት ልክ በተሽከርካሪው ወንበር ልክ መሆኑን መመረያው ያዛል፡፡

በዚህም መመሪያው ካስቀመጠው በላይ ለሚጭኑ ሚኒባሶች 1 ሺህ ብር፣ ለሀይገር፣ ለቅጥቅጥና ለአውቶቡስ 1 ሺህ 500 ብር፣ ለታክሲ (ላዳ፣ ሜትር ታክሲ) 500 ብር፣ ባለሦስት ወይም ባለአራት እግር ባጃጅ ወይም ሞተር ሳይክል 500 ብር ያስቀጣል ተብሏል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት የታሪፍ መጠን በተመለከተ ቀደም ሲል በሀገራዊ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት በተደረገው አዲስ የታሪፍ ጥናት ጭማሪ መሠረት የሚቀጥል ነው ብለዋል፡፡

የብዙኀን ትራንስፖርት ታሪፍን በተመለከተ አሁንም መንግስት እያደረገ ባለው ድጎማ የሚቀጥል እንደሆነም ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ማንኛውም የከተማዋ የትራንስፖርት ተሳፋሪ ወይም ተጠቃሚ፣ አሽከርካሪ እና ረዳት የፊት መሸፈኛ (ጭምብል) ማድረግ እንዳለባቸው የቢሮ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ሆኖም የፊት መሸፈኛ ወይም ጭምብል ያላደረገ ተሳፋሪ በተሽከርካሪ ላይ ማሳፈር ወይም የህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪ ላይ አገልግሎት ማግኘት እንደማይቻል ኢንጂነር ስጦታው አስረድተዋል፡፡

የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች የተሳፋሪውን ጤንነት ለመጠበቅ የሚረዳ የአየር ዝውውር በተሽከርካሪው መኖሩን ለማረጋገጥ የተሽከርካሪውን መስኮት መክፈት አለባቸውም ተብሏል፡፡

ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት አገልገሎት ተጠቃሚ፣ አሽከርካሪ እና ረዳት ወደ ተሽከርካሪ ከመግባታቸው በፊት የእጅ ንፅህና የሚጠብቁ አልኮል ወይም ሳኒታይዘር ወይም ውሃና ሳሙና መጠቀም እንዳለባቸውም ተጠቅሷል፡፡

መመሪያው ሁሉም በከተማዋ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ ጸረ ተሕዋሲያን ርጭት /ዲስኢንፌክት/ ማድረግ እንዳለባቸውም ያዛል፡፡

በተያያዘም በከተማዋ የስራ ሰዓት መውጫ ማለትም ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ድረስ ከምሽቱ 10፡00 እስከ 2፡00 ሰዓት ድረስ ማንኛውም ከባድ ተሽከርካሪ መንቀሳቀስ እንደማይችሉም ተገልጿል፡፡

በዚህ መሰረት በመመሪያው ላይ የተቀመጡትን ክልከላዎች በሚጥሱ አካላት ላይም መመሪያው የቅጣት ውሳኔ ተቀምጧል፡፡

ከታሪፊ በላይ ለሚያስከፍሉ ተሸከርካሪዎች በተመሳሳይ 1 ሺህ 500 ብር እንደሚያስቀጣ የተቀመጠ ሲሆን እና የኮቪድ 19 መከላከያ ተግባራትን አለማከናወን አሽከርካሪና ረዳት ማስክ ሳያደርጉ ከተገኙ 1 ሺህ ብር በሰው፣ የፊት መሸፈኛ ያላደረገ ተሳፋሪ በሚጭኑበት ወቅት ደግሞ 500 ብር (በሰው) ያስቀጣል ተብሏል፡፡

እንዲሁም ተሽከርካሪን ሳኒታይዝ አለማድረግ 2 ሺህ ብር፣ በስራ ሰዓት ያለ ሥራ ቆሞ የተገኘ ተሽከርካሪ ለታክሲ 1 ሺህ ብር፣ ለአውቶቡስ 2 ሺህ ብር፣ ለሀይገርና ቅጥቅጥ 1 ሺህ 500 ብር መስመር አለመሸፈን/ አለመስራት ወይም ሁለት እና ከሁለት ቀን በላይ በሳምንት ከስራ ሲቀር በመደበኛ የሚቀጡ ሲሆን ታፔላ ሳይሰቅል መስራት 1 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ነው ኢንጂነር ስጦታው ያስረዱት፡፡

አፈፃፀሙን በተመለከተም ትራንስፖርት ባለስልጣን፣ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ እና የትራፊክ ፖሊሶች ይቆጣጠራሉ እንዳስፈላጊነቱም እርምጃ እንደሚወስዱ መመሪያ እንደሚጠቅስ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.