Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለዐርበኞች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለዐርበኞች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

ሙሉ መልዕክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ለኢትዮጵያ ዐርበኞች ቀን እንኳን በሰላም አደረሳችሁ።

ይህ ቀን ጀግኖች ዐርበኞቻችን ሀገራችንን ከአምስት ዓመቱ የኢጣልያ ወረራ ነጻ ያደረጉበት ቀን መታሰቢያ ነው። ይሄንነ ቀን ስናስብ ከጀግኖች ዐርበኞቻቶን ሦስት ነገሮችን እየተማርን ነው። የመጀመሪያው ከምንም ነገር በላይ ሀገርን ማስቀደም ነው። በወቅቱ የነበሩት ሁሉም ዐርበኞች በንጉሡ አገዛዝ የሚደሰቱ፣የሚስማሙና የሚደግፉ አልነበሩም።

በመንግሥት አስተዳደር ቅሬታ የነበራቸው፣ የተገፉ፣ የተለያዩ አማራጭ የአስተዳደር ዘይቤዎችን የሚያቀርቡ ነበሩ። በንጉሡ ላይ ዐምጸው የሸፈቱም ነበሩ። በወቅቱ ጠላት እጁ ላይ ካለው አቅም ይልቅ አሸናፊ ያደርገኛል ብሎ ያሰበውን የኢትዮጵያውያንን ብሶትና ቅሬታ እንደ መሳሪያ ሊጠቀምበት ተንቀሳቅሶ ነበር።

ከንጉሡ ጋር የማይዋደዱና በሆዳቸው ቅሬታ የያዙትን በስልጣንና በማባባያ ዝም አሰኝቶ ኢትዮጵያን የመጨበጥ ፍላጎቱ ለማሳካት ሞከሯል። ነገር ግን ዐርበኞች ሁሉም ለሀገራቸው ከብር፣ ፍቅር እና የጸና ዐቋም ነበራቸው። ቅሬታቸውና ልዩነታቸው ከመንግሥት አስተዳደር ጋር እንጂ ከሀገራቸው ጋር አልነበረም። በዚህም የተነሣ በሉዓላዊነታቸው ሳይደራደሩ፣ ለፋሽስት ጥቅም ሳያጎበድዱ፣ የሀገራቸውን ነጻነት ለማስከበር ዱር ቤቴ ብለው ዘመቱ።

ሁለተኛው ለሀገር ማንንም አለመጠበቅ ነው። ለሀገር ለሚከፈል ዋጋ ማንም እንዲጠይቅ፣ እንዲያስተባብር ወይም እንዲቀሰቅስ አይጠበቅበትም። ሁሉም ዜጋ የሚያውቀውን፣ የሚያምነውንና የሚችለውን ለማድረግ በራሱ መንፈስ መነሣት አለበት። ዐርበኞቻችን ያስተማሩን ይሄንን ነው። በወቅቱ ንጉሡ ከሀገር ወጥተዋል። ሊያስተባብሩ የሚችሉ ተቋማትና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አልነበሩም። በዚያ ጊዜ ዜጎች ለሀገራቸው ራሳቸውን ነው ያስተባበሩት።

በጀት፣የሰው ኃይል፣ ቁሳቁስ አልጠየቁም። የሚሰጥ የለምና። ይዘው የወጡት የራሳቸውን መሣሪያ፣ የራሳቸውን ስንቅ እና ራሳቸውን ብቻ ነበር። ምናልባት ከስንቃቸው ጋር የሀገር ፍቅር በልባቸው ይዘው ስለወጡ እሱ ገመድ ሆኖ አስተሳስሯቸው እንደ አንድ ጦር ሆነው ጠላትን እንዲፋለሙ አድርጓቸው ይሆናል፤ ግን ለዚያ የሀገር ፍቅር የማንንም ቅስቀሳ ወይም የየትኛውንም ተቋም ውትወታ አላሻቸውም።

ሦስተኛው ትልቅ ቁም ነገር ሀገርን የሚታደገው የዜጎች አንድነት መሆኑ ነው። ዐርበኞች በየአካባቢያቸው በጎበዝ አለቃ እየተመሩ በመዝመት ትግሉን ጀምረውታል። ትግላቸው ፍሬ ማፍራት የጀመረው ግን በየአቅጣጫው የነበረው የዐርበኞቻችን ተጋድሎ እየተቀናጀና እየተናበበ ሲመጣ ነው። የሚችሉት በአካል፣ ያልቻሉት በመልእከት እየተገናኙ

አንድነታቸውን አጠናከሩ። የውስጥና የውጭ ዐርበኞች ተቀናጁ። ብሔር፣ ቋንቋና እምነት ገደብ ሳይሆንባቸው ሀገር አንድ አደረገቻቸው። ለአንዲት ሀገር በአንድነት ቆሙ። ይህም ፍሬውን በቶሎ እንዲለቅሙት አደረጋቸው። እኛ የእነዚህ ዕርበኞች ልጆች ነን። የእነዚህ ዐርበኞች ባለ ዕዳዎችም ነን። ሀገራችን በየዘመናቱ ዋጋ እየተከፈለባት እዚህ የደረሰች ናት። የምትቀጥለውም ዋጋ ስሚከፍሉ ልጆቿ ነው። እንደ ዐርበኞች እናትና አባቶቻችን ከምንም ነገር በላይ ሀገራችንን እናስቀድም።

ዐርበኞቻችንን ከባድ ዋጋ ያስከፈሏቸው ከለየላቸው ጠላቶቻቸው በላይ የሚመሳሰሏቸው ባንዳዎች ነበሩ። ዛሬም ዋጋ የሚያስከፍለን ባንዳነት ነው። ባንዳነት ሆገርን ለግል ጥቅም፣ ሕዝብን ለእለት እንጀራ፣ ሕሊናን ለተራ ቅያሜና ኩርፊያ ሲባል ያለ ማንገራገር መሸጥ ነው።

በሐሳብ፣ በአመለካከት፣ በርእዮት፣ በአሠራር ልዩነት ሊኖረን ይችላል። ብዝኃነት ስንል የሐሳብ ብዝኃነትንም ይጨምራልና።

የሐሳብ ብዝኃነት የሀገር ዕሴት እንጂ የሀገር ዕዳ መሆን ግን የለበትም። የምንቃወመው መንግሥት ይኖረን ይሆናል፤ የምንቃወማት ሀገር ልትኖረን ግን አትችልም። ሀገር እስይዘን ቁማር ልንጫወት የምንችለበት ምንም አማራጭ የለም። እኛ የዐርበኞቻችን እንጂ የባንዶች ልጆች አይደለንም።

ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ከማን ምን ይጠብቃል? ከማን ምን ይጠይቃል? ራሱን ለሀገሩ ለመስጠት እንጂ ሀገሩን ለራሱ ለመሠዋት ኢትዮጵያዊ የሆነ ማነው? በየትም ሀገር እንኑር፣ የትኛውም ሞያ ላይ እንሠማራ፣ ምንም ዓይነት ዐቅም ይኑረን፣ ግን ለኢትዮጵያ ጥቅም እስካላዋልነው ድረስ የዐርበኞች ልጅነታችን ትርጉም የለውም። ዐርበኞች ሞተውና ቆስለው ያወረሱንን ሀገር ባገኘነው አጋጣሚ አስውስንና አሳምረን ለልጆቻን ማሳለፍ ይገባናል። ያለን ጥቂት ዕቅም ሀገር ወዳድነት ሲጨመርበት ሚዛኑን ይደፋል። ያለን ውሱን ዕውቀት ኢትዮጵያዊ ወኔ ሲታከልበት ተአምር ይፈጥራል። ያለንበት ቦታና ኃላፊነት ቀላል መስሎ ቢታየንም፤ ለሀገር ለመሥራት አስበን ከተነሣን ትንሽዋም አስተዋጽኦችን ለኢትዮጵያ በትልቁ የምትመነዘር ናት።

ውድ ኢትዮጵያውያን፣

ዐርበኞቻቸን እንደነበሩበት ዘመን ዛሬም ኢትዮጵያ በውስጥ ባንዳዎችና በውጭ ጠላቶች መከራ እየተቃጣባት ነው። ይሄን ለሀገራችን የሚደገስ የመከራ ድግስ የምንቀለብሰው እና ወደ ጠላቶቻችን የምንመልሰው ከተቀናጀን፣ ከተባበርንና ከተናበብን ነው። በየዘርፉ የምናደርገው ሀገር የመታደግ ትግል ለአንዲት ኢትዮጵያ ትርፍ በሚያመጣ ዓላማ ካልተቀናጀ ሲሚንቶና ብረት እንዳጣ አሸዋ ይሆናል። የቆመ ቢመስልም ይወድቃል፤ ሕልውናችንም በቀላሉ አደጋ ያገኘዋል።

ስለዚህ በያለንበት፣ በምንችለውና በምናውቀው ነገር ሁሉ እንተባበር፤ ሊጋራ ሕልውናችን ተናብበን እንሥራ፤ ለአንዲት ሀገር አንድ እንሁን።

ሀገር የዐርበኝነት መንፈስ ትፈልጋለች። የዐርበኝነት መንፈስ ማለት ለሀገር የሚከፍሉት ዋጋ ከሀገር ከሚቀበሉት ነገር ሲበልጥ ነው። ዐርበኝነት የምንደኝነት ተቃራኒ ነው። ምንደኝነት ሀገርንም ጨምሮ ሁሉንም ነገር በጥቅም ብቻ መተመን ነው። ለመሆኑ ዐርበኞቻችን ለከፈሉት የሕይወት ዋጋ ምን ገንዘብ ይተመንለታል?

ለማንም ሳይሆን ለራሳችን ጥቅም ስንል ወደ ቀልባችን እንመለስ፤ የምንሠራው ሥራ ለነገ ስማችን፣ ለልጆቻችን፣ ለታሪካችን ምን ዓይነት መጥፎ ጠባሳ እንደሆነ ይግባን። ማንም ሰው ካላበደ በቀር የገዛ ቤቱን ለማፍረስ ከጠላቱ ጋር ኢያሴርም። ስለ ምንም ጉዳይ እንደራደር ይሆናል። ነገር ግን የመጨረሻ ምሽጋችንን አሳልፈን ለመስጠት፣ በሀገርና በቤታችን መደራደር የሞኞች ሁሉ ሞኝ አስመስሎ በጠላቶቻችን ፈት መሳቂያ መሳለቂያ እንደሚያደርገን ማወቅ አለብን። እንደ ብልሆቹ ዐርበኛ ወላጆቻችን በሴረኝነትና ባንዳነት ላይ ኮርተን “ጅሎች ነበሩ” በሚለው ፋንታ “ጀግኖች ናቸው” የሚል የከብር ስም እንያዝ። ከተሞኘን ሀገር ስለማይኖረን እንደ ተረት ንበሩ” መባላችን ጥርጥር የለውም፤ በተቃራኒው በጠላቶቻቸን ሴራ ሳንወድቅ ይሄን ከፉ ጊዜ በስኬት ካለፍን እንደ ዐርበኛ ወገኖቻችን “ጀግንነታችን” በመላው ዓለምእየተመሰከረለት፣ ትውልድ እያመሰገነን ይቀጥላል። ክብር፣ ይህችን ሀገር በነጻነት ላቆዩልን ዐርበኞች እናቶቻችንና አባቶቻችን ይሁን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሚያዚያ 26፣ 2013 ዓም

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.