Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል የህክምና ኦክስጂን ማምረቻ እና ማከፋፈያ ማዕከል አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የሶማሌ ክልል የህክምና ኦክስጂን ማምረቻ እና ማከፋፈያ ማዕከል አስመርቋል፡፡

ማዕከሉን በጅግጅጋ ከተማ የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን እና የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክር ዩሱፍ መሀመድ በጋራ መርቀው ከፍተዋል።

እንደ ክልል የነበረውን የህክምና ኦክስጂን እጥረትን እንደሚቀርፍ እና ከዚህ በፊት 622 ኪሎ ሜትር ርቀት አዲስ አበባ ድረስ ይኬድ የነበረውን ርቀትና ወጪ የሚቀንስ መሆኑም ነው የተገለፀው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ በምርቃ ስነ-ስርአቱ እንደገለፁት፤ የህክምና ኦክስጂኑ በዚህ ወቅት ስራ መጀመሩና መመረቁ በተለይ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ታማሚዎች ላይ እያጋጠመ ያለውን የመተንፈሻ ኦክስጅን እጥረትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀርፍ እና ሌሎች ተዛማጅ የሆኑ እንደ ልብ ህመም በሽተኞች አገልግሎቱ ይሰጣል ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዩሱፍ መሐመድ በበኩላቸው፤ ከክልሉ የቆዳ ስፋት አንፃር የህክምና ኦክስጅን ተደራሽነት ላይ የነበረውን ችግር እንደሚቀርፍ ጠቅሰው፣ይህ አሁን ስራ የጀመረው የኦክስጅን ማምረቻ ማእከል በቀን ወደ 200 ሲሊንደር ማምረት ስለሚችልና የክልሉን የኦክስጅን ፍላጎት እንደሚሸፍን ገልፀዋል።

በህክምና ኦክስጅን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከሉ ምረቃ ላይም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የክልልና የዞን ፣ የጤና ቢሮ አመራሮችና የተለያዩ የመንግስት የስራ ሐላፊዎች ተገኝተዋል።

ይህ በምስራቅ ኢትዮጵያ የመጀመርያው የሆነው የህክምና ኦክስጂን ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል በቀጣይ ከክልሉ ባለፈ ለአጎራባች ክልሎችም ተደራሽ የማድረግ አቅምና ፍላጎት መኖሩም ተገልጿል።

በክልሉ በሰፈነው አስተማማኝ ሰላም በርካታ የልማት ሥራዎች በመሠራት ላይ እንደሆነ መገለጹን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.