Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው ለሕዳሴ ግድብና ለገበታ ለሀገር 166 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮ በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ዳያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት  ከ166 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ዳያስፖራው በ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ136 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ድጋፉ የተሰበሰበው በቦንድ ሽያጭ፣ በስጦታና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህ በጀት ዓመት እስካሁን የተደረገው ድጋፍ ባለፈው በጀት ዓመት ከተሰበሰበው ገንዘብ ከ50 በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለውም ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ለግድቡ ግንባታ በአጠቃላይ 200 ሚሊየን ብር ከዳያስፖራው ለመሰብሰብ መታቀዱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በቅርቡ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ባደረገው ውይይት በዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ከ53 ሺህ ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንና 100 ሺህ ዶላር ለመስጠት ቃል መግባታቸውን አስታውሰዋል።

በተመሳሳይ በሚኒሶታና በሰሜን ማዕከላዊ የአሜሪካ ክፍል በሚገኙ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ የ40 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ዳያስፖራው ለግድቡ ከ50 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አማካኝነት ባለፈው ዓመት ይፋ በተደረገው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ዳያስፖራው እስካሁን 30 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም ነው ዋና ዳይሬክተሯ የገለጹት።

የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት ማብቂያ ድረስ ከዳያስፖራው ለ”ገበታ ለአገር” ፕሮጀክት 50 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን አመልክተዋል።

የ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶችን ዳያስፖራው እንዲያውቀው ፕሮጀክቶቹን የማስተዋወቅ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝና ዳያስፖራው ፕሮጀክቶቹን የመደገፍ ፍላጎት እንዳለውም ተናግረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.