Fana: At a Speed of Life!

“ጀግኖች አርበኞች ኢትዮጵያን አናስደፍርም ብለው እንዳለፉ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ይህን ታሪክ መድገም አለበት”-አፈጉባኤ ታገሰ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ጀግኖች አርበኞች ኢትዮጵያን አናስደፍርም ብለው እንዳለፉ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ይህን ታሪክ በመድገም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት የሚፈታተን ማንኛውንም ኃይል በጋራ ቆመው መመከት ይገባቸዋል ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጠቅላይ መመሪያን ጎብኝቷል።

በዚህ ወቅት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ አየር ኃይል በተቋሙ እያደረገ ባለው የለውጥ ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋሙን ለመቀየር ጥረት ማድረጉን በጉብኝታቸው ገልፀዋል።

የአየር ኃይሉ በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ገልፀው ተቋሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኃይሉን በቴክኖሎጂና በመሰረተ ልማት ለማደራጀት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ የጀመረውን ስራ ይበልጥ ማጠናከርና የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ርብርብም ሁሉም ተባብሮ ከዳር ማድረስ እንዳለበት አሳስበዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትም ሆነ አየር ኃይል ትልቁ እሴቱ ከራስ በላይ ለህዝብና ሀገር መሆኑን የጠቀሱት  አፈጉባኤው ጥንት አባቶችም ይሄንኑ እሴት አንግበው ለአገራቸው እንደተዋደቁ ነው የተናገሩት።

የጥንት አባቶች ከራስ በላይ ለአገር ብለው በቂ ቴክኖሎጂና መሳሪያ ባልነበረበት የውጪ ወራሪ ኃይል መመከታቸውን ነው የገለፁት።

ይሄ ለአሁኑ ትውልድም ሆነ ለቀጣዩ አስተማሪና የኢትዮጵያዊያን ስነ ልቦና ከፍ እንዲል ያደረገ ነው ብለዋል።

ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው፣ በማንነታቸው የሚኮሩ፤ አልደፈር ባይ ስብዕና ያላቸው እንዲሆኑ ያስቻለው የጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ጀግኖች አርበኞች ኢትዮጵያን አናስደፍርም ብለው እንዳለፉ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ይህን ታሪክ በመድገም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት የሚፈታተን ማንኛውንም ኃይል በጋራ ቆመው መመከት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከማንኛውም ኃይል ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን ለመመከት ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ናቸው።

በለውጡ አመታት የአየር ኃይሉን በማዘመን ረገድ አመርቂ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው በዚህም አገራዊ ሰራዊት የመገንባት ስራ መሰራቱን ነው የተናገሩት።

“ሰራዊት ሀገር እንጂ ብሄር የለውም” በሚል ሰራዊት ውስጣዊ አንድነቱን ይዞ አገራዊ ፍቅር ሰንቆ እንዲሰለጥን ትልቅ ስራ በመሰራቱ በህግ ማስከበር ዘመቻ ውጤት መጥቷል ብለዋል።

በዝግጁነት ደረጃም ትልቅ አገርና ህዝብ የሚመጥን አየር ኃይል ለመገንባት እየሰራን ነው ብለዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.