Fana: At a Speed of Life!

በ499 ትምህርት ቤቶች የሚተገበረው የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም  ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በ499 ትምህርት ቤቶች የሚተገበረው የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም  ይፋ ሆኗል።

የትምህርት ሚኒስቴር ከህፃናት አድን ድርጅት  ጋር በገባው ውል የተቀናጀ አካታች ሀገር በቀል የምገባ ፕሮግራም ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አካሂዷል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም አማራጭ ሳይሆን ትውልድን የማስቀጠል የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ይህ የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም በመማር ማስተማሩ ሂደት የተማሪዎችን ተሳትፎ ከማሳደግ ባሻገር እንደ ሀገር ውጤታማና ንቁ ዜጎችን በፍትሃዊነት ለማፍራት የሚያግዝ መሆኑንም ሚኒስቴር ዴኤታው ገልፀዋል፡፡

የሀገር በቀል ምገባ ፕሮግራሙ በተለይም በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት የተጎዱ ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙና በትምህርታቸውም ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያግዛቸውም ነው የተነገረው፡፡

የሲዳማ ክልል ም/ር/መስተዳድር እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በሪሶ በበኩላቸው÷ የምገባ ፕሮግራሙ የትምህርት ቤቶችን ውስጣዊ ብቃት እና የተማሪዎችን ተሳትፎን  የሚያሳድግ መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሮግራሙ በተለያየ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱና ሌሎችም ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ከማድረግና ፍትሃዊነትን ከማረጋገጥ አንፃር  ወሳኝ መሆኑም  ተነግሯል።

ፕሮግራሙ በክልሉ ውስጥ የተሳካ እንዲሆንና ቀጣይነት እንዲኖረው የክልሉ መንግስት የሚቻለውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም  አቶ በየነ በሪሶ  ተናግረዋል።

የህፃናት አድን ድርጅት በኢትዬጵያ ዋና ዳይሬክተር ኢኪን ኦጉቶጉላሪ በበኩላቸው÷ የተቀናጀ አካታች ሀገር በቀል የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በ499 ትምህርት ቤቶች የሚተገበር መሆኑን እና የምገባ ፕሮግራሙ ህፃናት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ የሚረዳ  መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የምገባ ፕሮግራሙን እውን ለማድረግም  ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኤጁኬሽን በተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት  2 1ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የተቀናጀ አካታች ሀገር በቀል የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በአምስት ክልሎች የሚተገበር ሲሆን በአጠቃላይ 499 በላይ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም 163 ሺ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል መባሉን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.