Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ200 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 29 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ200 ሚሊየን ዶላር (8 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር) የብድር ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
የብድር ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ እና የዓለም የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ተጠሪ ኦስማን ዲዮን ተፈራርመውታል፡፡
የብድር ገንዘቡ በዋነኝነት ኢትዮጵያ በ10 አመቱ መሪ የልማት እቅድ ላለመችው መጠነ ሰፊ የልማት ግብ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ተግባራዊ ለማድረግ የሚውል ሲሆን ይህም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በቴሌኮሙዩኒኬሽን መስክ ስራ በመፍጠርና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የዲጂታል ኢኮኖሚ ስትራቴጂውን እውን የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል፡፡
ይህ የኢትዮጵያ ዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት የሚል ስያሜ የተሰጠውና በብድር ገንዘቡ ተግባራዊ ሊደረግ የታቀደው ፕሮጀክት ከፈረንጆቹ ሚያዝያ 21 ቀን 2021 እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2026 ማለትም ለአምስት አመታት ያህል የሚዘልቅ መሆኑን ከገንዝብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የፕሮጀክቱ ዋንኛ አላማዎችም የዲጂታል ቴክኖሎጂ አካታችነት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዋጋ ተመጣጣኝነትና የዲጂታል ስራ ፈጠራ ናቸው፡፡
በዚህ መሰረት በዲጂታል ቴክኖሎጂ አካታችነት የሀገሪቱ የኢንተርኔት ተደራሽነትና የተጠቃሚዎች ቁጥርና ስብጥር እንደሚያድግ፣ በዲጂታል ቴክኖሊጂ ዋጋ ተመጣጣኝነት ረገድም ለዲጂታል አገልግሎት የሚከፈለው ወርሀዊ ክፍያ ተመጣጣኝ እንደሚሆን እንዲሁም በዲጂታል የስራ ፈጠራ ዘርፍ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚፈጠሩ የስራ መስኮች የሚስፋፉበትና ዘላቂነታቸው የሚረጋገጥበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠርም ታውቋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.