Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ መላው ህዝብ እጅ ለእጅ በመያያዝ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ችግሮችን በፅናት እንዲቋቋም ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጠባቂ ሳህለወርቅ ዘውዴ መላው ህዝብ እጅ ለእጅ በመያያዝ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ችግሮችን በፅናት እንዲቋቋም ጥሪ አቀረቡ፡፡

ፕሬዚዳንቷ በነገው እለት የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀን ምክንያት በማድረግ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የፕሬዚዳንቷ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል

 የተከበራችሁ የአገራችን ህዝብ፣
 በመላው አለም የምትኖሩ የሰብዓዊነት ደጋፊ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች
 የተከበራችሁ የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ቤተሰቦች፣
 ክቡራትና ክቡራን

ከሁሉ አስቀድሜ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ሚያዝያ 30 ለሚከበረው የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ቀን እንኳን አደረሳችሁ፣ እንኳን አደረሰን እላለሁ፡፡
በዚህ ዓመት የቀይ መስቀል ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ #Unstoppable በሚል መሪ ቃል ለ74ኛ ጊዜ ሲከበር፣ በአገራችን ደግሞ ‘’ፅናት’’ በሚል መሪ ቃል ለ63ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡

መሪ ቃሉ በመላው ዓለም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተጎዱ ሰዎችን የሚታደጉ በጎፈቃደኞች፤ ሠራተኞች፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ በችግሮቹ መጠንና ስፋት ሳይበገሩ ሰብዓዊ
ተግባራቸውን የሚወጡት፣ የሚያጋጥሟቸው የርዕዮተ አለም፣ የዕምነት፣ የፖለቲካ፣ የዘርና የፆታ ልዩነቶች ሣይበግሯቸው (#Unstoppable) መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡

መሪ ቃሉ የተመረጠው የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ አባላትም ሆኑ ደጋፊዎች ለሰብዓዊ ክብር ትኩረት በመስጠት፣ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን ያለ አድልዎ፣ በገለልተኝነትና የአሰራር ነፃነታቸው ተጠብቆ፣ የተረጂዎችን ህይወት ለመታደግ ኑሯቸውንም መልሶ ለማቋቋም ቅድሚያ የሚሰጡት ለሰብዓዊነት ባላቸው ‘ፅናት’ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡

በአገራችን እለቱን የምናከብረው፣የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች የማኅበሩን በጎፈቃደኞች፣ አባላት፣ ሠራተኞች፤ የንቅናቄውና ሌሎች አጋሮቻችን በኮቪድ-19ና በአንበጣ ወረርሽኝ፤ በጎርፍ፣ በእሳትና በመሬት መደርመስ አደጋዎች፣ አልፎ ተርፎም በግጭትና በጎሳ ነውጦች የተቸገሩ፤ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉና ከስደት የተመለሱ ወገኖቻችንን ህይወትና ኑሮ ለመታደግ2 የህይወት መስዋዕትነትን ጨምሮ ለከፈሉት ዋጋ ፣ በፅናት ለሰብዓዊነት ያሳዩትን ቁርጠኝነት ለማስታወስና የሰብዓዊነት አርማቸውን አንግበን፣ አላማቸውን ለማስቀጠል ነው፡፡

በዚህ አጋጣሚ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ችግሮችን በጽናት ተቋቁመው ሰብዓዊ አገልግሎት ሲያበረክቱ ህይወታቸውን ላጡ በጎፈቃደኞች ያለኝን ክብር በመግለፅ፣ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ፡፡

የዘንድሮውንም የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ ቀን የምናከብረው ከወትሮው የተለየ ወቅት ውስጥ ሆነን ነው ። በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ዜጎች ውድ ህይወታቸውን ያጡበት ፣ ዜጎች ከቄያቸው ልጆች ከቤተሰባቸው የተለያዩበት ከባድ ወቅት ነው።

ማህበሩ በግንባር ቀደምትነት ወገኖቻችንን ለመታደግ ያደረገው ከፍተኛ ጥረት የሚደነቅ ነው ። ይሁን እና የችግሩ ስፋት ከሚገመተው በላይ ነው። ሕዝባችን ላይ የሚደርሰውን መከራ ቢያንስ መቀነስ ፣ ቢቻል ማላቀቅ የቀይ መስቀል ማህበር ተልእኮ ቢሆንም እንደዚህ መሰል ችግር ውስጥ እንዳይገባ አስቀድሞ መከላከልን ባህል ማድረግ ይጠበቅብናል።

ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በሰብዓዊ ሥራዎች የመንግስት አጋዥ በመሆን ለሰማንያ ስድስት አመታት የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ የሰብዓዊነት መርሆዎችን መሠረት በማድረግ ችግሮች በሚከሰቱባቸው ስፍራዎች ሁሉ ቀድሞ መገኘት የሚያከናውናቸው ሰብዓዊ ተግባራት መበረታታት እና መደገፍም ያለበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት፣ አጋር ድርጅቶች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ በመላው አለም የምትኖሩና ሰብዓዊነትን የምትደግፉ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እያበረከተ ላለው ሰብዓዊ ተግባር ላደረጋችሁት አስተዋጽዖ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ እና በራሴ ስም እያመሰገንኩ፣ ዛሬም እንደትናንቱ፣ ወደፊትም እንደዛሬው እጅ ለእጅ ተያይዘን የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ችግሮቻችንን በፅናት እንድንቋቋም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ ።

ፅናትና ቅድሚያ ለሰብዓዊነት!
ለሰብዓዊነት እንኖራለን!
አመሠግናለሁ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.