Fana: At a Speed of Life!

የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚሰራው ስራ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚሰራው ስራ ትኩረት እንዲሰጠው ጠየቀ።

የዘርፉ ምሁራን እንደሚገልጹት በኢትዮጵያ በህይወት ከሚወለዱ 1 ሺህ ጨቅላ ህጻናት መካከል 33ቱ ለህልፈት ይዳረጋሉ።

ይህም በፈረንጆቹ 2016 ከነበረውና ከ1 ሺህ ጨቅላ ህጻናት መካከል ከሚከሰተው የ29 ህጻናት ህልፈት አንጻር ጭማሪ ያሳያ ሲሆን፥ ይህም በአመት ከ100 ሺህ በላይ ጨቅላ ህፃናት ህይወታቸውን ያጣሉ ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ ባለፉት 10 አመታት የእናቶችን ሞት መቀነስ ቢቻልም፥ የጨቅላ ህጻናትን ሞት ጭማሪ አሳይቶ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።

ችግሩን ከመሰረቱ ለመረዳት እና የመፍትሄ አማራጮችን ለመጠቆም የፖሊሲ ገለጻ መዘጋጀቱን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥ የኢንስቲቲዩቱ ባለሙያዎች ከጤና ሚኒስቴር፣ ተመራማሪዎች እና በዘርፉ ላይ ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት የመጡ ተወካዮች በተገኙበት ምክክር መካሄዱን ገልፀዋል።

የጨቅላ ህፃናት መታፈን፣ ኢንፌክሽን እና ጊዜያቸው ሳይደርስ የሚወለዱ ህፃናት ለጨቅላ ህፃናት ሞት ዋነኛ ምክንያት ተብለው መለየታቸውም ተገልጿል።

በተጨማሪም የቅድመ ወሊድ ክትትል አለማድረግ ፣ በጤና ተቋማት አለመውለድ፣ ቢወለወዱም በቂ እና ጥራት ያለው አገልግሎት አለማግኘትና ሌሎችም ምክንያት ተብለው ተለይተዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎትን ማጠናከርና የተለያዩ አደረጃጀትን መጠቀም እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ስራን ማጠናከር፣ የወሊድ ክትትሉን ተያያዥነት ባለው መልኩ ከቅድመ እርግዝና ጀምሮ ማጠናከርና በየደረጃው ለሚሰጠው አገልግሎት የጥራት ደረጃ ማስቀመጥ፣ ከግብአት አቅርቦት እና መሰረተ ልማት ጋር የተገናኙ ችግሮችን መፍታት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ተብለው መለየታቸውንም ገልፀዋል።

ከጨቅላ ህፃን ሞት ጋር በተገናኘ ያለውን የተዛባ አመለካከት መቀየር ይገባል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፥ ከ10 አመቱ መሪ የልማት እቅድ ጋር የተናበበውና በ2030 የጨቅላ ህጻናትን የሞት ምጣኔ አሁን ካለበት ወደ 12 ለማውረድ የተያዘውን አቅድ ለማሳካት መንግስትና ባለድርሻ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሃብታሙ ተክለስለሴ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.