Fana: At a Speed of Life!

ጠላቶቻችንን በግራ እጃችን እየጠበቅን በቀኝ እጃችን  እየሰራን  መሆን አለበት- ጠ/ሚ ዐቢይ

 

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሞጆ- መቂ- ባቱ የመንገድ ፕሮጀክት መርቀው ከፍተውታል፡፡

በክፍያ መንገዱ ምርቃት ስነስርዓት ላይ ዶክተር ዐቢይ አህመድ፥ የምንፈልጋትን ሃገር  ለመገንባት ጠላቶቻችንን በግራ እጃችን እየጠበቅን በቀኝ እጃችን  እየሰራን መሆን አለበት ብለዋል።

ዶክተር ዐቢይ አሁንም ባሉ ፈተናዎች ተስፋ ሳንቆርጥ ጠላቶችንን ተስፋ እያስቆረጥን ሪቫን እየቆረጥን እንቀጥላለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዛሬ ያሉትን በርካታ ችግሮችን በመመልከት ዜጎች ለውጡን እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋልም ነው ያሉት ዶክተር ዐቢይ።

ዶክተር ዐቢይ ዛሬ የተመረቀው መንገድ በቅርቡ ለምርቃት ከበቃው የሞያሌ ሃዋሳ መንገድ ጋር በመሆን ለኢኮኖሚው  እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።

ለፕሮጀክቱ ስኬት የፋይናንስ ድጋፍ ያደረጉትን ለአፍሪካ ልማት ባንክና ለኮርያውን ኤግዚም ባንክ አመስግነዋል።

የትራንስፖርት ሚንስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው ለመንገዱ ደህንነት መጠበቅ ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢ/ር ሃብታሙ ተገኝ የግብርና ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ፣ ለቱሪዝም ዘርፉ ማደግ እንዲሁም ለሃዋሳ እና የቡልቡላ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች የመንገዱ መጠናቀቅ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

ለፕሮጀክቱ ስኬት አስተዋጽኦ  ላበረከቱ  ነዋሪዎች እና ሌሎች አካላትም ኢ/ር ሃብታሙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ፕሮጀክቱ 92 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን ከሞጆ መቂ 56.4 ኪሎ ሜትር ፣  ከመቂ ባቱ 37 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፣ አተጠቃላይ መንገዱ 32 ሜትር ስፋት አለው።

ፕሮጀክቱ የአፍሪካ ቀንድ ትስስር /Horn of Africa integration initiative/ አካል ሲሆን ኢትዮጵያ ከቀጠናው ሃገራት ጋር ላላት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል በጅቡቲ ወደብ ላይ ተንጠልጥሎ የቆየውን የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ምርቶች እንቅስቃሴ አማራጭ በማስፋትም ኢትዮጵያ የላሙ ወደብን በስፋት እንድትጠቀም  የመንገዱ ግንባታ ድርሻው የጎላ ይሆናል።

መንገዱ የአዲስ አበባ -ሞያሌ- ናይሮቢ- ሞምባሳ የመንገድ አካል ሲሆን 10 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና ከግብጽ ካይሮ ተነስቶ ደቡብ አፍሪካ  ኬፕታውን ድረስ የሚዘልቀው የትራንስ አፍሪካ ሃይዌይ የመንገድ ትስስር አካል ነው።

የመንገዱ መገንባት ለአህጉር አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስርም የበኩሉን የሚወጣና  ቀጣይ ክፍል የሆነው የባቱ አርሲ ነገሌ ሐዋሳ የመንገድ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።

በመንገድ ምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የደቡብ ብሔሮች ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ርዕስ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ እንዲሁም የትራንስፖርት ሚንስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ተገኝተዋል።

በምስክር ስናፍቅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.