Fana: At a Speed of Life!

ከተማ አስተዳደሩ ትናንት ለተፈጠረው የአደባባይ ኢፍጣር መርሐግብር መስተጓጎል ይቅርታ ጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንብት 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትናንት ለተፈጠረው የአደባባይ ኢፍጣር መርሐግብር መስተጓጎል ይቅርታ ጠይቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “ትናንት ለተፈጠረው ነገር በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ አደባባዮች የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ አንድ ማዕድ በጋራ የተቋደሰ ህዝብ የኔ፣ የኔ በሚል በአንድ አደባባይ አይጣላም” ሲሉ አክለዋል፡፡

የአደባባይ ኢፍጣር መርሐግብሩ የተስተጓጎለው “ወቅታዊ የደህንነት እና የጸጥታ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የቦታው ስፋት እና ርዝመት ውስን እንዲሆን ባቀረብነው ሀሳብ አዘጋጅ ኮሚቴው ባለማመኑ ብቻ” መሆኑንም አንስተዋል።

“የትናንት ምሽቱ የጸጥታ አካላት እንቅስቃሴም የሁሉም ነዋሪዎች ሰላም እና ደህንነት እንዲረጋገጥ አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ ያለመ እንጂ በፍፁም የኢፍጣር ክልከላ” አለመሆኑን ገልፀዋል።

ለአብነትም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ሌሎች የኢፍጣር መርሐግብሮች መካሄዳቸውን ጠቅሰዋል።

“ይሁን እንጅ አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው አካላት ይህን ጉዳይ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ በማህበራዊ ሚዲያ ሊያራግቡት ሞክረዋል” ነው ያሉት ምክትል ከንቲባዋ።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ በተፈጠረው ሁኔታ የተሰማውን ቅሬታ የገለጸበት መንገድ ጨዋነት የተሞላበት እና ሰላማዊ እንደነበር በመግለፅም አድናቆታቸውን ችረዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.