Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም አቅደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በአዲስ አበባና በአዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ሁከት፣ ሽብርና ትርምስ በመፍጠር ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ የውጭ እና የውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚደገፉ የሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ ሴራ ወጥነው ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንዳሉ በጋራ ግብረ ኃይሉ በተደረገባቸው ጥብቅና የተቀናጀ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይህን እኩይ የጥፋት ሴራ ለመፈጸም ከውጭ በተለያዩ አካላት በሚደረግላቸው የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎች ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የሸብርተኞቹ የህወሓትና የሸኔ ቡድን አባላት ከከባድ እስከ ቀላል የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን ከመሰል ጥይቶች፣ ቦምቦችና ተቀጣጣይ ቁሶች ጋር ለጥቃት ሊጠቀሙባቸው ያዘጋጇቸው ቢሆንም፤ የታቀደውን የጥፋት ተልዕኮ ማክሸፍ መቻሉን መግለጫው አትቷል።

መግለጫው አክሎም ለሽብርተኞቹ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና በሌሎችም አካባቢዎች ጭምር የተለያዩ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች በህገወጥ መንገድ ሊተላለፉ እንደነበር ጠቁሞ፥ በተደረገ ጥብቅ ክትትልና ፍተሻም ለጥፋት ተልዕኮ መፈፀሚያቸው ሊጠቀሙበት የነበረ ከ305 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እና ከ2 ሚሊየን በላይ የኢትዮጵያ ብር መያዙን አስታውቋል፡፡

መግለጫው እንዳብራራው ይህንን የጥፋት ተግባር ለመፈፀም ቀደም ሲል ትግራይ ድረስ ታጣቂዎቹን መልምሎ በመላክ ከሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ በንፁሃን ዜጎች ላይ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን ሲፈፅም የቆየው የአሸባሪው የሸኔ ቡድን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን ሲያገኝ እንደቆየና በቡድኑ ላይ የመንግስት ፀጥታ አካላት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰዱት ባለው ተከታታይ እርምጃ እየተዳከመና ከባድ ኪሳራ እያጋጠመው መምጣቱን ተከትሎ መሰረተ ልማቶችን እንዲያወድሙ እንዲሁም በታዋቂ ሰዎች፣ በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና በዜጎች ላይ በተደራጀና በተጠና መንገድ ግድያ እንዲፈፀሙ አባ ቶርቤ በሚል የሰየማቸውን የከተማ ክንፍ አሸባሪዎች ወደ ተለያዩ ከተማዎች አሰማርቶ ነበር ብሏል፡፡

ለእነዚህ የሽብር ቡድኖች የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን፣ ቦምቦችን፣ ለፍንዳታ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሶችን እንዲሁም ሰነዶችን በስውር ለመስጠት ሲያጓጉዙ የነበሩ በርካታ የቡድኑ ተጠርጣሪ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አመላክቷል፡፡

ከተጠርጣሪዎች መካከልም አብዲሣ ጣፋ ቆጮልቴ እና ኤብሣ ተረፋ ቶኮሣ የተባሉት ግለሰቦች ከአማራ ክልል ሁመራ አካባቢ በኮድ ሁለት የታርጋ ቁጥር A70977-አ.አ ሚኒባስ መኪና የውስጥ አካል የተለያዩ የጦር መሳሪዎችንና ጥይቶችን ሰግስገውና ደብቀው መዳረሻቸውን ምዕራብ ኦሮሚያ አድርገው በደሴ በኩል አዲስ አበባ ሊገቡ ሲሉ ለገጣፎ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።

በተመሳሳይ አርጆ አለማየሁ ዋቆ የተባለች የሸኔ ቡድን አባል ሶላር የተገጠመላቸው ዓለም አቀፍ የሳተላይት ስልኮችን በሞያሌ በኩል በማስገባት ወደ ተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በድብቅ ለማሰራጨት ስትሞከር ቡራዩ ከታ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሏን የጠቆመው የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ፥ ራቢራ ዊርቱ ሞሲሳ፣ ደረጄ ዱጋሳ ሆርዶፋ እና ወንደሰን መግራ ታደሰ የተባሉ ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላትም ተጨማሪ የሳተላይት ስልኮችን ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት ሲሞክሩ በነበረው ሚስጥራዊ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቅሷል፡፡

ሸብርተኛው የሸኔ ቡድን በተደራጀና በተጠና መንገድ ግድያ እንዲፈፅሙ አዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ያሰማራቸው የአባ ቶርቤ ቡድን አባላት ተመሳስለው ጥቃት የሚፈፅሙባቸው የመከላከያ ሰራዊት የቀድሞ ደንብ ልብሶችንና እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ጭምር በድብቅ ሲጓጓዙ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫው አትቷል።

አበራ ሙለታ፣ለሊሳ አዳሙ፣ አበራ ጌታ፣ ሙሌ ስዩሜ እና አብርሃም አቡ የተባሉ የቡድኑ አባሎችና የድርጊቱ ተዋናዮች እንዲሁም አሽከርካሪውና ረዳቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጫውም ጠቁሟል፡፡

የሽብር ቡድኑ በጅማ ከተማ ጥቃት ለመፈጸም ስምሪት የሰጣቸው ኢያሱ ለማ፣ ካሊድ ሰይድ፣ አብደላ አባ በላይ፣ ሰይፉ በላይ እና ነጋሳ ኬኔሳ የተባሉ ተጠርጣሪዎችም ከታጠቋቸው የእጅ ቦምቦችና እና ሽጉጦች እንዲሁም ከሌሎች የጥፋት ተልዕኮ መፈጸሚያ ቁሶች ጋር መያዛቸውንም ነው ያመላከተው፡፡

በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩና ለአሸባሪው የሸኔ ቡድን የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎች የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ያመላከተው የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይሉ፥ እነርሱም ጀምበሩና አበበ አሜሪካ፤ ገመቹ፣ አብደላ እና ተርፋ አውስትራሊያ ዱጋሳ ኖርዌይ እንዲሁም ቶለሺ ታምሩ ወይም ገቢሴ፣ ገመቹ አቦዬ፣ ለማ ረጋሳ ወይም ቢቂላ እና ጃራ ቱለማ ኬንያ እንደሚኖሩም አውስቷል፡፡

እነዚህን የሽብር ቡድኑን እንቅስቃሴ እየደገፉ ያሉትን በድምሩ 15 ተጠርጣሪዎችን ማንነት በማጣራትም ለህግ ለማቅረብ ከወዳጅ ሀገራት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጾ፥ በሀገር ውስጥ እስካሁን የቡድኑን የሽብር እንቅስቃሴ ለመግታት በተወሰደው እርምጃ የቡድኑን የከተማ ህዋስ አባላትን ጨምሮ 71 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል፡፡

መግለጫው አያይዞም ለሽብር ቡድኑ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ የ80 ተጠርጣሪ ግለሰቦች የገንዘብ ስርዓት እንዲቋረጥ የተደረገ መሆኑን እያሳወቀ፥ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቡድኑ ዋና ዋና የገንዘብ አስተላላፊ ተብለው የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል፡፡

ሌሎችንም በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመላክቷል፡፡

ከአሸባሪው የሸኔ ቡድንና ከሌሎች ፀረ-ሰላም ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረው የሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የፈፀመውን የሀገር ክህደት ወንጀል ተከትሎ፥ መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ የቡድኑ ቁልፍ አመራሮች እርምጃ ሲወሰድባቸውና ገሚሶች ደግሞ እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲሰጡ ጥቂት የታጠቁ የቡድኑ ሃይሎች በተንጠባጠበ መልኩ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀሱም ነው የገለጸው፡፡

ቡድኑ የተወሰደበትን ተከታታይ እርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ “ክብሪት” የሚል መጠሪያ የሰጠውን ገዳይ ቡድን በክልሉ ዋና ዋና ከተሞችና በአዲስ አበባም ጭምር ለማሰማራት መሞከሩንም አትቷል፡፡

በአሜሪካ የሚኖሩ ጀኔራል ፍስሃ ማንጁስ ካህሳይና ወዲ ምጉላት የተባሉ ግለሰቦች በሆላንድ የሚኖሩ ተክላይ እና አታክልቲ፣ እንግሊዝ የሚኖረው ታከለ፣ ስዊድንና ደቡብ ሱዳን የሚኖሩት ተስፋይ ንጉስና ሰይፈ አምባዬ የተባሉ ተጠርጣሪዎች ሽብርተኛውን የሕወሓት ቡድን በገንዘብ የሚደግፉ መሆናቸው በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን በመግለጽ የጋራ ግብረ ኃይሉ ግለሰቦቹን በህግ ተጠያቂ የማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው ያስታወቀው፡፡

በሀገር ውስጥ ሆነው ለቡድኑ የገንዘብና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርጉ የነበሩ 32 የቡድኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም እና በቡድኑ ለሽብር ድርጊቱ ሊውሉ የነበሩ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች፣ የሬዲዮ መገናኛዎች እና ሌሎች ተቀጣጣይ ቁሶችም መያዛቸውን ጠቁሟል፡፡

እነዚህ ሽብርተኛ ቡድኖች ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት ሀገሪቱን ወደ ሽብርና ትርምስ ውስጥ በማስገባት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ሴራ ወጥነው ለመንቀሳቀስ እየሞከሩ ቢሆንም የደህንነትና የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በቅንጅት በመስራት ሴራቸውን አስቀድሞ ማክሸፍ መቻሉን የጋራ ግብረ ሃይሉ ገልጿል።

የሸኔና የህወሓት ሽብርተኛ ቡድን አባላት በመንግስት ጸጥታ ሀይሎች እየተወሰደባቸው ባለው ተከታታይ እርምጃ፥ በርካታ የቡድኑ አባላት መደምሰሳቸውንና መያዛቸውን እንዲሁም ለሽብር ተልዕኮ የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች፣ የእጅ ቦምቦች፣ ለፍንዳታ የሚውሉ ተቀጣጣይ ቁሶችና ሰነዶች መያዛቻውን አስታውቋል።

ይህን ተከትሎም የሽብር ቡድኖቹ ከፍተኛ ኪሳራና የስነልቦና ጫና ውስጥ መግባታቸውን መግለጫው አንስቷል፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ የውስጥና የውጭ ጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀናጅተው ሀገሪቱን ወደ ለየለት ትርምስ ለመክተትና ለማፍረስ እየሰሩ ቢሆንም፥ በርካታ ሴራዎችን አስቀድሞ በማወቅ ማክሸፍ መቻሉንና የትኛውም ሴራ ከመንግስት እንዲሁም ከደህንነትና ጸጥታ አካላት እይታ የተሰወረ አለመሆኑንም አስታውሷል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማካሄድ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገች ባለችበት በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የውጭ ሀይሎች በቀጥታ ከሚደርስባት ጫና ባሻገር፤ ከተመቻቸው በጥቂት ተላላኪዎቻቸው የሸኔና የህወሓት ሽብርተኛ ቡድኖች ጥቃት በመሰንዘር ካልተመቻቸው በህቡዕ የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር ሀገሪቱ ወደ ትርምስ እንድትገባ የተለያዩ እኩይ ሴራዎች እየተጠነሰሱ መሆናቸውን ህዝባችን ሊገነዘብ ይገባል ብሏል የጋራ ግብረ ኃይሉ በመግለጫው፡፡

በመሆኑም ህዝባችን ሰላሙንና ደህንነቱን ለመጠበቅ እንዲሁም የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ሴራዎቹን በማክሸፍ ለአፍታም አይን በማያስከድን ስራ ላይ የተሰማሩ የመረጃና ደህንነት እንዲሁም የጸጥታ ተቋማትና አካላትን የተቀናጀ እንቅስቃሴ በመደገፍ እያደረገ ላለው ትብብር የጋራ ግብረ ኃይሉ ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

ተመሳሳይ ሀገር የማፍረስ እኩይ ሴራዎችን በማክሸፍ በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በቀጣይ ለህዝቡ የማሳወቅ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን መግለጫው አረጋግጧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.