Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጀፍሪ ፊልትማን ጋር ተወያዩ።

ውይይታቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።

አቶ ደመቀ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔዎች በተለይም በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና መልሶ ማቋቋም ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን በተመለከተ፣ መጭውን ብሔራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ለማድረግ ስለተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ በድርድር እልባት እንዲያገኝ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ፍላጎት በተመለከተ ለልዩ ልዑኩ አስረድተዋቸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት በማንሳት፥ በሁለቱ ሃገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አምባሳደር ጀፍሪ ፊልትማን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፥ በሰላምና መረጋጋት ጉዳዮች በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት አንስተዋል።

አያይዘውም የታላቁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድርን በማስቀጠል በሁሉም ተደራዳሪ አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ላይ ለመድረስ በሚደረገው ጥረት በአሜሪካ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.