Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ለመኸር ከሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ግማሹ ወደ ክልሉ ገብቷል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በ2013/14 ምርት ዘመን መኸር ወቅት ከሚያስፈልገው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ወደ ክልሉ መድረሱን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ብርሀነ አርዓያ እንደገለፁት በምርት ዘመኑ የመኸር ወቅት ክልሉ 800 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ያስፈልገዋል።
ከዚህ ውስጥ 400 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መድረሱን ገልጸዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለክልሉ የማዳበርያ መግዥያ በሰጠው የ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የብድር ዋስትና መሰረት ማዳበሪያው እየቀረበ መሆኑን ምክትል የቢሮ ሃላፊው አስታውቀዋል።
ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም አመላክተው የህብረት ስራ ማህበራት መጋዘኖቻቸውን የማዘጋጀትና የአርሶ አደሩን የማዳበሪያ ፍላጎት የመለየት ስራዎች መከናወናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በየወረዳው የሚገኙ የእርሻና ገጠር ልማት መዋቅሮችን ዳግም የማደራጀት ስራም መካሄዱን የጠቆሙ ሲሆን በዚህ ሳምንት ውስጥ ማዳበርያውን ወደ ወረዳዎች የማጎጎዝ ስራ እንደሚጀመር አመላክተዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ለምርት ወቅቱ ከሚያስፈልገው ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ውስጥ የ150ሺህ ኩንታል ግዥ ተፈጽሞ ወደ ክልሉ እየተጓጓዘ መሆኑን ተናግረዋል።
የምርጥ ዘር ግዥው በፌደራል መንግስትና በሌሎች አካላት መፈጸሙን ምክትል የቢሮው ሀላፊው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.