Fana: At a Speed of Life!

የሴቶችና ህጻናት ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴቶችና ህጻናት ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል የጋራ ስምምነት በስካይ ላይት ሆቴል  ተፈረመ።

ስምምነቱ  የተፈረመው  በሴቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ  ፖሊስ ዩኒቨርስቲ እና በተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ድርጅት መካከል መሆኑ  ተመላክቷል።

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር  ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ ÷ መንግስት ጾታዊ ጥቃትን ያለመታገስ መርህን በመከተል ትልልቅ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ጾታዊ  ጥቃትን በመከላከልና ምላሽ በመስጠት በደንብ የሰለጠነ ልዩ አቅምና ችሎታ ያለው የፖሊስ ኃይል ያስፈልጋልም ነው ያሉት ፡፡

እንደ  ሚኒስትሯ ገለጻ ጾታዊ ጥቃትን ያለመታገስ ስራ የተቋሙ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ አንዱ ስራ በመሆኑ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመው÷ ከተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ድርጅት (ዩኤንኤፍፒኤ) በተገኘ የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ የሴቶችን ጥቃት የሚከላከል  የፖሊስ ግብረ ኃይል በማሰልጠን  ወደስራ የማስገባት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ግብረ ኃይሉን የማቋቋም ስራውም በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ ሌሎች ክልሎች የማስፋት ስራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስነ-ህዝብ ድርጅት ተወካይ ወይዘሮ  ደንያ ጌይል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን በማስታወስ  ጾታዊ ጥቃትን ላለመታገስ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም አድንቀዋል።

ዛሬ በሚደረገው ስምምነት አማካኝነት ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል ረገድ የአቅም ግንባታውን እንደሃገር ከመስራት ባሻገር በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ሃገራትም ጭምር ጥራት ያለውና በአርዓያነት የሚጠቀስ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ማየት እንደሚሹ  ገልጸዋል፡፡

በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ጀነራል ዘላለም መንግስቴ  በበኩላቸው ÷ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና በሃገራችን ካሉ ደንቦችና መመሪያዎች በመነሳት ፖሊስ ሲሰለጥን የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር በተለይም ለሴቶችና ህጻናት ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ይህንኑ አጠናክሮ ለመቀጠል እንዲህ ያለው ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑን አንስተው÷ በተቋማቸውም በኩል አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝደንትና ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው÷ እንደ ፖሊስ ማህበረሰባችንን ከማንኛውም ጥቃት ለመጠበቅ ኃላፊነት ወስደን እየሰራን ቢሆንም ያሉብንን የበጀትና የስልጠና ክፍተቶች ለመሙላት አጋር ድርጅቶች ተቋማችንን ለመደገፍ ከጎናችን በመሆናችሁ ላመሰግን እወዳለሁ ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.