Fana: At a Speed of Life!

የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሐግብር  በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰላም የአንድነት የፍቅር እና የመተሳሰብ ኢፍጣር መርሐግብር  በአዲስ አበባ ተካሄደ።

የጎዳና ላይ ኢፍጣር ፕሮግራሙ  ከሜክሲኮ እስከ ባምቢስ ባለው መንገድ በደማቅ ሁኔታ ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር የዛሬው ተግባር በሃገራችን ከዚህ ቀደም ያልታየ ስለሆነ በጣም ደስ የሚል ዝግጅት ነው ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙ እውን እንዲሆን ላደረጉት አካላት ለአዘጋጆቹ፣ ለአዲስ አበባ መስተዳድር እና ለጸጥታ ኃይሎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ለአንድነት፣ ለሰላም እና ለፍቅር እንድትቆሙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡

በኢፍጣር ስነስርዓቱ ወቅት በመጪው ምርጫ ሁሉም እንዲሳተፍ ያሳሰቡት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ሃገራችን ሰላም ያድርግልን ወደ ልማት የምትጓዝ ያድርግልን ሲሉ ዱኣ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይም ንግግር ያደረጉ ሲሆን ለኢድ ዋዜማ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙ ባለመናበብ ምክንያት ሳይካሄድ ቢቀርም ዛሬ ባማረ መልኩ ለመካሄድ በቅቷል ነው ያሉት፡፡

በመዲናችን በቀላሉ እሳት መጫር ይቻላል ብለው ለሚያስቡ አካላት እንደማይሳካ የሃይማኖት አባቶች ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሃይማኖታዊ ስርዓቶች የሁላችንም ሃብቶች ናቸው ያሉት ተአቶ ጃንጥራር ሁላችንም ልንጠብቃቸው ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የፕሮግራሙ አዘጋጆች ሃላል ፕሮሞሽንና የነጃሺ በጎ አድራጎት ድርጅት በበኩላቸው በአንድነት፣ በሰላምና በፍቅር የኢፍጣር ፕሮግራም ላይ የተሳተፉትን ምዕመናን አመስግነዋል፡፡

የዝግጅቱ ዓላማ ረመዳን ቅዱስ ወር የመተዛዘን የመደጋገፍ ወር መሆንን ጠቅሰው ከአቅመ ደካሞች ጋር በጋራ ለማሳለፍ ያለመ የአብሮነት ፕሮግራም መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡

ሁለተኛው የዝግጅቱ አላማ ከዚህ ቀደም በግብጽ በ7 ሺህ ሰው የተያዘውን የጎዳና ላይ ኢፍጣር ክብረ ወሰን ለማሻሻል ያለመ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

እንዲሁም ሁሉም ሙስሊም አብሮ በማፍጠር በአንድ ልብ ዱዓ የሚያደርግበት እንዲሆን ያለመ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም ፕሮግራሙ በየዓመቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.