Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም  ”ቴሌብር ” የሞባይል የክፍያ  ስርዓትን  በይፋ  አስጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮ ቴሌኮም ”ቴሌብር ” የሞባይል የክፍያ ስርዓት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በወዳጅነት አደባባይ እያካሄደ ነው።
የኢትዮ ቴሌኮም ”ቴሌብር ” የሞባይል የክፍያ ስርዓትን የዕለቱ የክብር እንግዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በይፋ አስጀምረውታል።
የቴሌብር የክፍያ ስርዓት የአየር ሰዓት ለመሙላት እና ሌሎች አገልግሎቶች ክፍያዎችን ለመፈጸም ያስችላል ተብሏል።
የክፍያ ስርዓቱ የሞባይል ኔትወርክ ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ በየትኛውም የስልክ ቀፎ አይነት መጠቀም ያስችላል ነው የተባለው።
ቴሌብር በኪስ እንደሚያዝ ገንዘብ ቦርሳ፣ ገንዘብን ለመያዝ፣ ለመላክና ለመቀበል እንዲሁም ክፍያን በሞባይል ለመፈጸም እንደሚያስችል ተገልጿል።
በዚህም የክፍያ ስርዓት ደንበኞች ካሽ ወይም ቼክ ሳያስፈልጋቸው ዘርፈ ብዙ ክፍያዎችን እንዲፈፅሙ ያደርጋል ተብሏል።
ይህም በሀገር ውስጥ እንዲሁም በ ዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም የትስስር መንገዶች ላይ ገንዘብ መላላክን፣ ለዕቃና አገልግሎቶች ግዢ የሚደረጉ ክፍያዎችን መፈፀም ያስችላል።
ከዚያም ባለፈ ከሀገር ውጪ ካለው ዳያስፖራ ገንዘብ ለመቀበል፣ ገንዘብ ለመቆጠብ፣ ብድር ለማግኘት እና የባንክ አካውንት ከቴሌብር ጋራ እንዲተሳሰር የሚፈቅድ መሆኑ ተመላክቷል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ እስከዛሬ ኩባንያችን ባለፉት 127 ዓመታት ካቀረባቸው አገልግሎቶች ለየት ያለውን የቴሌ ብር አገልግሎት በማቅረባችን እንኩዋን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ቴሌ ብር በገጠር የሀገሪቱ ክፍል እና በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመደገፍ እና ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓን ለመዘርጋት አጋዥ መሆኑን አመላክተዋል።
የቴሌኮም መሰረተ ልማት በመስፋፋቱ በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይህ መተግበሪያም በአምስት ቋንቋዎች እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ40 አስከ 50 በመቶ በቴሌኮም ዘርፍ  እንዲንቀሳቀስ እንሰራለን ብለዋል ሃላፊዋ።

በመርሃ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.