Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የሚሲዮኑ ጊዜያዊ ኃላፊ ፊሊፕ ቦቨርዲን ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ ደመቀ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ድርጅት በኢትዮጵያ በሚፈጠሩ ሰው ሰራሽ ግጭቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ግንባር ቀደም በመሆን እያበረከተ ስላለው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሚሲዮኑ ኃላፊ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ ለማስኬሄድ የበጀት ጭማሪ ለማድረግ ዕቅድ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ እስረኞችንና ተፈናቃዮች መጎብኘታቸውንም ለአቶ ደመቀ አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ከቤኒሻንጉል፣ ከትግራይ እና ከኦሮሚያ ክልሎች ተፈናቅለው በሃገሪቱ የተለያየ ስፍራ ለሚገኙ እርዳታ ፈላጊዎች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የስራ ሃላፊው ቀይ መስቀል እስካሁን በትግራይ ክልል ያከናወናቸው ተግባራት ላይ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው ፤ እርምት የሚፈልጉ ጉዳዮችን አቅርበዋል፡፡

በትግራይ ክልል የሰብአዊ ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ደመቀ፥ በሁለተኛው ዙር ለ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ መደረጉን እና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እርምጃዎች እንደሚወሰድ አስረድተዋል፡፡

የፀጥታ ስጋት ባሉባቸው ውስን ቦታዎች ጭምር መከላከያ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ድጋፍ እየተደረገ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.