Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለኢድ አልፈጥር የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕስ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 442ኛው የኢድ-አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

“በዓሉን ስናከብር የመተጋገዝና አብሮ የመኖር ዕሴቶች ይበልጥ እንዲያድጉና፥ የመረዳዳት፣ የመደጋገፍና የመከባበር መንፈስ ይጎለብት ዘንድ በመስራት ሊሆን ይገባልም” ነው ያሉት፡፡
የእምነቱ ምሰሶ የሆነውን የተቸገሩትን መርዳትና መደገፍ እንዲሁም ለሐቅና ለእውነት መቆምን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ህዝበ ሙስሊሙ ባለፉት 30 ቀናት በጾምና ጸሎት ማሳለፉን በመጥቀስ የረመዳን ወር ከፈጣሪ ምህረት የሚለመንበት፣ መረዳዳት የሚጠናከርበትና በጎ ተግባራት የሚስፋፋበት ወር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በረመዳን ወር የሚታዩ መልካም ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው እዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በተያያዘም የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለመላው የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 442ኛው የዒድ-አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ የመጣውን የኮሮና ስርጭትን በማሰብ በጥንቃቄ እንዲያከብርም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

እስልምናን ጨምሮ ሁሉም ሃይማኖቶች መሰረታቸው ሰላም በመሆኑ በሃይማኖቶቹ ውስጥ ያሉ መልካም እሴቶችን በመጠቀም ለሰላም ሁሉም ዘብ መቆም ይገባልም ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

በተጨማሪም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ለኢድ አልፈጥር የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ የብሔር እና መሠል ግጭቶች መነሻ ምክንያቶች በመንግስት ጥረት እየተቀረፉና መፍትሄ እየተሰጣቸው ሲሄድ ጠላቶቻችን ደግሞ የሀይማኖት አጀንዳን እያነሱ ሊያጋጩን ይሞክራሉ ብለዋል።

በመሆኑም እምነቶችን መሰረት አድርገው ሊከፋፍሉን የሚፈልጉ ሀይሎችን በመታገል ሰላምና ወንድማማችነትን እንዲሁም መቻቻልን የበለጠ ለማጠናከር ተጋግዘን መስራት ይኖርብናልም ነው ያሉት።

የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው፥ ሁሉም ምዕመን በቅዱሱ የረመዳን ወር ሲፈፅም የቆየውን የመተሳሰብና የመረዳዳት ተግባር ከበዓሉ በኋላም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥትም የዒድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልእክት፥ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን የተቸገሩትን በማሠብ፣ በመረዳዳት እና በአብሮነት እንዲያከብረው ጥሪ አቅርቧል።

የሀረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር የተከበሩ አቶ ኦርዲን በድሪ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ ህዝብ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያዳበረውን መልካም ነገርን አብዝቶ የመስራት ዝንባሌ ከረመዳን ወር በኋላም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.