Fana: At a Speed of Life!

መቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያጎላ ነው – የእስልምና እምነት ተከታዮች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ያለው ኢትዮጵያዊ አንድነት ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል አርአያና ተምሳሌት መሆኑን በማዕከሉ ድጋፍ የሚደረግላቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ተናገሩ።

በረመዳን ጾም ወቅት የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖች ያሳዩት የወንድማማችነት መንፈስ የጎላ እንደነበርና በፍጹም ቤተሰባዊነት ጾሙም ሆነ በዓሉ በመካሄዱ መደሰታቸውንም ገልጸዋል።

ማዕከሉ 1 ሺህ 442ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ በስሩ ያሉና ድጋፍ የሚደረግላቸውን የእስልምና እምነት ተከታዮችን ጾም አስፈትቷል።

በበዓሉ ላይ የታደሙ የእምነቱ ተከታዮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ማዕከሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊና የሁሉም እምነት ተከታዮች ቤትና መኖሪያ እንደሆነ መስክረዋል።

በጾም ወቅትም ሆነ በዛሬው የበዓሉ ዕለት ኢትዮጵያዊ አንድነት የጎለበተበትና ሃይማኖትንና ብሔርን መሰረት አድርገው ለግጭት ለሚጋበዙ ዜጎች ምሳሌና አርአያ የሚሆን ነው።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ኡስታዝ አብራር መሃመድ በማዕከሉ ላሉ የእምነቱ ተከታዮች የሃይማኖት መምህር መሆናቸውን ገልጸው፤ “ሜቄዶንያ የተለያዩ ብሔረሰቦችና የተለያዩ እምነት ተከታዮች ፍላጎታቸው ተጠብቆ የሚኖርበት ነው” ብለዋል።

በማዕከሉ የሚኖሩ ሁሉም ተረጂዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ አብረው እንደሚኖሩ የሚያምኑና ይህንንም በተግባር የሚያሳዩ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የዘንድሮው የኢድ በዓልና የትንሳኤ በዓል አከባበር የዚህ ማሳያ እነደነበር አንስተው፤ በትንሳኤ በዓል ወቅት የእስልምና እምነት ተከታዮች አብሮነታቸውን ያሳዩበት እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁንም በዚህ በኢድ-የጾም ወቅትም ሆነ በበዓሉ እለት ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ተዋዶ፣ ተከባብሮ አንዱ ለሌላው አጋርነቱን አሳይቶ የተከበረበት በመሆኑ ማህበረሰቡ ከማዕከሉ ብዙ የሚማረው አለ ሲሉ ያብራራሉ።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ፋጡማ አህመዲን በበኩላቸው በማእከሉ የሁሉም እምነት ተከታዮች መረዳዳትና መተጋገዝ የጎላ መሆኑን ገልጸው፤ ማእከሉ ለሚያደርግላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ማእከሉ ተግባሩን በስፋት ለማስቀጠል የበጎ ሰዎችን ድጋፍ እንደሚፈልግ አመልክተዋል።

የማእከሉ መስራችና ስራ አስኪያጅ ብንያም በለጠ “ማእከሉ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ እኩል እንደሆነ በጽኑ የሚያምንና በተግባር የሚያሳይ ነው” ብሏል።

“የጊዜ ጉዳይ ሆኖ በማእከሉ ያሉ ተረጂዎች ሁሉም የራሳቸው ህይወትና የተሻለ የኑሮ ደረጃን ያሳለፉ በመሆናቸው ፍላጎታቸውን ማሟላት ላይ ጥረት ይደረጋል” ብሏል።

በተለይም በሃይማኖታቸው ከፈጣሪያቸው ጋር የሚማከሩበት ለፈጣሪያቸው የሚጸልዩበትና የሚያመሰግኑበት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ላይም እንዲሁ።

በበዓል ወቅት ሁሉም ሳይከፋቸው በህብረት ተደስተው እንዲያሳልፉ ማዕከሉ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

ከኮቪድ-19 በፊት የነበረው የማህበረሰብ፣ የተቋማትና የተለያዩ አካላት ድጋፍና ጥየቃ በአሁኑ ወቅት እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ ሁሉም አካል ባለው አቅም ለማዕከሉ ያለውን አጋርነት እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል።

በግቢው ውስጥ የተጀመረውን ህንጻ ለማጠናቀቅና ተጨማሪ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ለማገዝ ድጋፍ የሚጠይቅ በመሆኑ በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ መጠየቁንም ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.