Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን አሁን ያለውን የኮቪድ 19 ስርጭት ለመግታት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገለፁ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)አሁን ያለውን የኮቪድ 19 ስርጭት ለመግታት ሁሉን አቀፍ ምላሽ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 ሀገር አቀፍ ንቅናቄን አስጀምረዋል።
ንቅናቄው የብሄራዊ የኮቪድ 19 ግብረሃይል፣ የክልል ርዕሰ መስተዳደሮች እና ከተለያዩ ሴክተር መስርያ ቤቶች የተገኙ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት አስጀምረዋል።
አሁን ያለውን የኮቪድ 19 የስርጭት ሁኔታ እየተገበርነው ባለው የምላሽ አካሄድ መፍታት ስለማይቻል ምላሹን ከጤና ሴክተር ባለፈ ሁሉን አቀፍ ምላሽን ማጠናከር፣ የአመራርና የህብረተሰቡን ትኩረትና ተሳትፎ ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ ለሁለት ወራት የሚቆይና በርካታ ዝርዝር ተግባራትን ያካተተ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ምላሽን ማጠናከር የሚያስችል ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 በሚል አገር አቀፍ ንቅናቄ አስጀምረዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ለሁለት ወራት የሚቆየውን ዳግም ትኩረት ለኮቪድ-19 አገር አቀፍ ንቅናቄ ዝርዝር እቅድ ያቀረቡ ሲሆን አሁን ላይ ያለዉ የቫይረሱ ስረጭት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዉ የኮቪድ 19 ስርጭት መቀልበስና የሞት መጠንን መቀነስ ፣ የዘርፈ ብዙ ምላሽን ማጠናከር ፣ የኮቪድ-19 ጽኑ ህክምና ተደራሽነት ማሳደግ፣ የተቀናጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የህግ ማስከበር ንቅናቄዎችን ማከናወን፣ የምርመራ ዓቅምና የክትባት ሽፋንን ማሳደግ ላይ ትኩረት በመስጠት ይሰራል ብለዋል፡፡
በንቅናቄዉም የቤት ለቤት ዳሰሳ ስራ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አጠቃቀም ተግባራዊ ማድረግ፣ አካላዊ ርቀት አተገባበርን መከታተል፣ እለታዊ አማካይ የመመርመር አቅምን ከፍ ማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወቅታዊዉን አለምአቀፍና አገር አቀፍ የኮቪድ 19 ሁኔታን ከግንዛቤ ዉስጥ በማስገባት በየደረጃዉ ያለዉ አመራርና የሚመለከተዉ አካላት ሁሉ ለንቅናቄዉ ስኬት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በቅንጅት ህብረተሰቡን በማሳተፍ መስራት ይጠበቅበታል ማለታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በተጨማሪም የሚዲያ አካላትና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ከኪነጥበብ ባለሙያዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ህብረተሰቡን ማንቃትና ቫይረሱ እያስከተለ ያለዉን ጉዳት ማሳወቅ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸው የተቀመጡ ክልከላዎችን ተከታትሎ ማስፈጸምና የተቀመጡ መመሪያዎችን ሳያሟሉ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ላይ አስፈላጊዉ እርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.