Fana: At a Speed of Life!

ሰላም፣ እርጋታ እና የዜጎች ደህንነት ለኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ እድገት ወሳኝ ናቸው – በአሜሪካ የህዝብ ዲፕሎማሲ አማካሪ ምክር ቤት

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 9 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላም፣ እርጋታ እና የዜጎች ደህንነት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ እድገት ወሳኝ መሆናቸውን በአሜሪካ የህዝብ ዲፕሎማሲ አማካሪ ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የድጋፍ መግለጫውን አውጥቷል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት ሰቅዘው ከያዟት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ለመላቀቅ እና ለሁሉም ዜጎቿ አስተማማኝ የሆነ የልማት መሰረት ለመጣል የሞት-የሽረት ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ገልጿል።

የመንግስት መዋቅር ክፉኛ በተዳከመበት ሁኔታ ላይ ሃላፊነቱን የተረከበው የለውጥ አመራር የተጋረጠበት ፈተና ቀላል አለመሆኑን እንደሚገነዘብ ጠቁሟል።

ይህ የለውጥ ሂደት እንዳይሳካ በውስጥና በውጭ የተደራጁ ግለሰቦች እና ቡድኖች በ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ብሂል ሕዝብን በዘውግና በእምነት በመከፋፈል እና አገርን በመበተታተን ላይ ያተኮረ ዕኩይ አላማቸውን ለማሳካት ከውጭ ጠላት መንግስታት ጋር ተባብረዋል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው እነዚህ ኃይሎች የሃገራችን ሕዝቦች በህይወታቸው ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡትን ሃይማኖት ከመጠቀም አልፈው ከውጭ ኃይሎች እና መንግሥታት ጋር በማበር ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈው ከመስጠት የማይመለሱ ናቸው ብሏል።

በአሁኑ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በምትመራበት ህገመንግስት መሰረት ስልጣንን ከምርጫ ውጭ የመያዝ ጥያቄ የህገመንግስት መሰረት የሌለውና ሕገ-ወጥ በመሆኑ፤ የሽግግር/የአደራ መንግስትም ሆነ ሌላ አይነት የመንግስትነት ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ፅኑ አምነታችን በመሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በማጤን፤ ምርጫውን፤ ነጻ፤ ፍትሃዊ፤ አሳታፊ፤ በተለይም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በማድርግ ሁሉም የመምረጥና የመመረጥ መብት ያለው ዜጋ መንግስትን “በምራጫ ሂደት ከመመስረትና ከመምራት” ውጭ የምርጫ እቀባም ሆነ ሌላ አላስፈላጊ ጫና ማድረግም ሆነ ምርጫን ማወክ ሀገርቱን ለማረጋጋትም ሆነ ለዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ምንም ፈይዳ የሌላቸው አሉታዊ ተግባሮች ናቸው።
የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ በዚህ አስቸጋሪ ፖለቲካዊና ማህበራዊ የፈተና ወቅት ሁኔታዎች በፈቀዱት መጠን የሚያደርገዉን ከፍተኛ ጥረት በመገንዘብና በመደገፍ፤ ማንኛውም ለኢትዮጵያና ለመላው ዜጎቿ በጎ የሚመኝ ግለሰብና ቡድን ይህንን የዲሞክራሲ ሂደት ማበረታታት አለበት ነው ያለው።

የሕዳሴ ግድብን የሁለተኛውን የውሃ ሙሌትም ሆነ ኢትዮጵያ በድንበሯ ውስጥ የሚገኘውን ውሃ የመጠቀም ሉዐላዊ መብት ያላት መሆኑን በማያሻማ ደረጃ በመደገፍ፤ የሱዳንና የግብፅ መንግስታት ኢትዮጵያ ውሃውን እንዳትጠቀም፤ ሕዳሴ ግድብን ስኬታማ እንዳታደርግ የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጫና፤ ጣልቃ ገብነትና የውክልና ጦርነት አደጋዎች እንደሚገነዘብም ነው የገለጸው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ባለችበት ነበራዊ ሁኔታ ይህ ብሄራዊ ምርጫ ሊኖረው የሚችለውን ህጋዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ሃገራዊ ፋይዳ ከግምት በማስገባት ከምንወስደው ገንቢ ሚና ውጭ፤ በዘውግ፤ በእምነት፤ በግል ጥቅምና በሌላ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌለን መሆኑን እየገለፅን ፤ የኢትዮጵያን ሰላም፤ እርጋታና ፍትሃዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችንና ሂደቶችን ለማደናቀፍ የሚፈታተኑ ድርጊቶችን የመመከት የግልና የጋራ ብሄራዊ ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ መወጣት ያስፈልጋል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ በአገር ቤትና በውጭ ለሚኖሩ ወገኖች የሚከተሉትን የአደራ ጥሪዎች አቅርቧል፤

1. በተለያዩ የሃይማኖት ጥያቄዎች ሰበብ ሕዝቦችን እርስ በእርሳቸው ለማጋጨት የሚደረጉሙከራዎችን በንቃት በመከታተል ከእነዚህ ድርጊቶች እንዲቆጠብና እንድንከላከል፤

2. በማናቸውም ሃይማኖት ተከታዮች የሚነሱ ኃይማኖታዊ ጉዳዮችና ጥያቄዎች አግባብነት ባለው ሁኔታ እንዲቀርቡ እና እንዲስተናገዱ እንዲደረግ፤ የኃይማኖት ተከታዮች፣የሃይማኖት አባቶች፣ የየሃይማኖት አስተዳዳሪዎች ወይም ኃላፊዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ግዴታቸውንና ሃላፊነታቸውን በቅንነት እንዲወጡ አደራ እንላለን።

3. መጪው አገራዊ ምርጫ የአገራችንን የዲሞክራሲ መሠረት የምንጥልበት መሆኑን በመገንዘብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ሙሉ ድጋፍ የምንሰጠው መሆኑን እየገለጽን፤ ሁሉም አካላት በሕግ አግባብ በምርጫው በመሳተፍ እንዲሁም አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ ለምርጫው ስኬታማነት ድርሻውን እንዲወጣ የአደራ መልዕክት አስተላልፏል።

4. በዚህ አጋጣሚ፤ ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ሂደትም ሆነ ከምርጫው በኋላ የሚፈጠር ቅሬታ ቢኖራቸው በህጋዊ ሂደትና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መንፈስ፤ የተቋማትን ገለልተኝነት ጠብቀው ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የዴሞክራሲ ሂደት ግንባታን እንዲያስተጋቡ እንጠይቃለን።

5. ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ መላው ኢትዮጵያውያን እንዳለፈው ከፍተኛ ጥረትና ድጋፍ ሁሉ በገንዘብም ሆነ የኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም ሉዐላዊ መብት በልዩ ልዩ መንገዶች፤ ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በመጠቀም ለዓለም መንግሥታት እና ሕዝቦች በማስገንዘብ ሙሌቱ እንዳይካሄድ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያከሽፉ ያልተቆጠበ ጥረት እንድናደርግ ብሄራዊና አገራዊ ግዴታችን እንድንወጣ አደራ እንላለን።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ የህዝብ ዲፕሎማሲያዊ አማካሪ ምክር ቤት
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.