Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለሱዳን የሽግግር መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ በተዘጋጀው ጉባዔ ላይ ተሳተፉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፈረንሳይ ለሱዳን የሽግግር መንግሥት ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ በፓሪስ ባዘጋጀችው ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
ጉባኤው ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተሳተፉበት መሆኑ ተገልጿል።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሀገራቸው ሱዳን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተበደረችውን እዳ ለማቃለል ያግዛታል ያሉትን 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ማክሮን ጥሪ አቅርበዋል።
ሱዳን ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ ሊሆን በሚችል የዴሞክራሲ ልምምድ ውስጥ ትገኛለች ያሉት የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ለሀገራቱ ትብብር እና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ በተካሄደ ውይይት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ስላለው ዘመናትን የተሻገረ እና በደም የተሳሰረ ወዳጅነት እና የሕዝቦች ትስስር አንስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተም ግድቡ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ኢትዮጵያ የዜጎቿን የኃይል ፍላጎት ከሟሟላት ባሻገር የቀጠናውን ሀገራትንም ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል መልኩ እየተገነባ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ከሱዳን ጋር በድንበር ጉዳይ የተፈጠሩ አለመግባባቶችም ሆነ ማንኛውም ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶች ሊፈቱ የሚገባው በውይይት እና በመርሕ ላይ ተመሥርቶ ሊሆን እንደሚገባው አፅዕኖት ሰጥተው መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡
በስብሰባው ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተጨማሪ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲም ከአፍሪካ ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.