Fana: At a Speed of Life!

ግብፅና ሱዳን በአባይ ወንዝ ላይ የያዙት አቋም ዓለም አቀፍ ሕግን የተቃረነ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብፅና ሱዳን በአባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ፖሊሲ ላይ የያዙት አቋም ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የተቃረነ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ “የሁለቱ አገሮች አቋም በኢትዮጵያ ላይ የውሃ የበላይነትን መጫን ነው” ብለዋል።

“ለአብነትም ግብጽ ከ150 ዓመታት በፊት የአባይ ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን በኃይል ለመቆጣጠር ስለመሞከሯ፣ በከፊልም የጣናን አካባቢ ለመያዝ ጥረት ማድረጓን” አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ባለው ሕገ መንግስቷም ግብፅ የናይል ወንዝ ብቸኛ ታሪካዊ ባለቤት ስለመሆኗ በይፋ አስቀምጣለች ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንዳትለማ ዓለም አቀፍ ጫና በማድረግ ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ መስራቷንም አስታውሰዋል።

ግብጽና ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ያላቸው አቋም ከግድቡ ግንባታ ጋር ሳይሆን የአባይን ውሃ በብቸኝነት የመጠቀም ፖሊሲ እንደሆነና ይህም ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር እንደሚቃረን ነው አምባሳደር ኢብራሂም ያስረዱት።

በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አገሮች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በመጠቀም ውስጣዊ አለመረጋጋት እንዲኖርና የተለያዩ ጫናዎችን ለመፍጠር እየጣሩ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሁለቱ ሀገራት ዓላማ “ኢትዮጵያን የውሃ መብት ማሳጣት በመሆኑ ድርድሩንም ሌሎች ወገኖች እንዲገቡ ብሎም አስገዳጅ ስምምነት በሚል አቋማቸውን እየለዋወጡ ይገኛሉ” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ውሃው የጋራ ሃብት በመሆኑ አጠቃቀሙ ፍትሐዊና ምክንያታዊ መሆን እንደሚገባው እንደምታምንና በዚሁ መርህ እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ኢትዮጵያዊያን ያለ ልዩነት ለስኬቱ በጋራ ሊቆሙ ይገባልም ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ የሶስትዮሽ ድርድር ቡድን አባል ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጥራትና ደህንነት ሁለቱ አገሮች የተስማሙበትና የፈረሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ ደህንነት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላና ጥራቱንም አስመልክቶ ያሉ መረጃዎችን ግብጽና ሱዳን በግልጽ እንዲያውቁ መደረጉን ተናግረዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ ክንውን አሁን ላይ 79 ነጥብ 9 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.