Fana: At a Speed of Life!

ከመተከል ዞን የተፈናቀሉ የአማራና የአገው ተወላጆችን ወደ ነበሩበት ለመመለስና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ስምምነት ተደረሰ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመተከል ዞን የተፈናቀሉ የአማራና የአገው ተወላጆችን ወደ ነበሩበት ለመመለስና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጋራ ስምምነት ላይ ደረሱ።

በዚህም ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ የፀጥታ ደህንነታቸውን የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ በተወሰኑ ውስን ቦታዎች ብቻ እንዲሰፍሩ በማድረግ በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፀጥታ አካላት በቅንጅት ለዜጎች የደህንነት ዋስትና መረጋገጥ እና በሚመለሱበት አካባቢ በመከላከያ ሠራዊት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችሉ የእለት እርዳታ ምግብ አቅርቦት ፣ የመጠለያ ቤት ግንባታ ፣ የእርሻ ግብዓቶች፣ የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት በሁለቱ ክልሎች በቅንጅት እንደሚሟላም ተጠቅሷል ።

በስምምነቱ መሰረት ከሁለቱ ክልሎችና ከፌደራል መንግስት የሚጠበቁ የጋራ እና የተናጠል ድጋፎች ወደ ፊት ተለይተው እንደሚቀመጡ ተነግሯል።

የተፈናቀሉ የአማራ እና የአገው ተወላጆችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ላይ የአማራና የቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልሎች የሠላምና የልማት የጋራ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት እንዲቋቋም በሁለቱ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ስምምነት ላይ ተደርሷል ።

ይህንን የሚያስተባብር ግብረ ሃይልም ሁለቱ ክልሎች ከሚመለከታቸው ቢሮዎች የሰው ሀይል የሚመድቡ ሲሆን በቀጣይነት ለማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የሚያስፈልገው ሎጅስቲክስ ፣ የሰው ሃይልና በጀት በሁለቱ ክልሎች መንግስታት ለመሸፈን ስምምነት ላይ መደረሱን ከአማራ ክልል ሠላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ስምምነቱ የአማራንና የአገው ተወላጆችን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝቦች ጋር ከዚህ ቀደም እንደነበረው የህዝቦችን በሠላም አብሮ የመኖር ባህላዊ እሴት የሚያጎለብትና ለዘመናት አብረው የኖሩ የወንድማማች ህዝቦችን ግንኙነት የሚያጠናከር እንደሚሆን ተጠቁሟል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለተፈፃሚነቱ ከመንግስትና ከተፈናቃዮች ጎን በመሆን ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም አስተዋፅጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.