Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ 30 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተባባሩት ዓረብ ኢሚሬቶች መንግስት ድጋፍ አማካኝነት ዋዲ አልሲደር ኮመርሻል ኢንቨስትመንት ሊያቢሊቲ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር በከተማዋ 30 ሺህ ወጪ ቆጣቢ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከዋዲ አልሲደር ኮመኘርሻል ኢንቨስትመንት ሊያቢሊቲ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ተወካዮች ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ የውል ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ ወቅትም ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ÷ በከተማዋ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ለማጣጣም የተለያዩ አማራጭ የቤት ልማት ፕሮግራሞችን በመንደፍ እና ተግባራዊ በማድረግ ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩም እንደ አንድ አማራጭ ካስቀመጣቸው ተግባራት መካከል ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና በመስራት ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን በአጭር ጊዜ በመገንባት ለተጠቃሚዎች ማድረስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የቤት ፍላጎቱን ለሟሟላት በሀገር ውስጥ እና ከውጪ ሀገር ኩባንያዎች ጋር በመቀናጀት በከተማዋ ከአንድ ሚሊየን በላይ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት እቅድ መያዙንም ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሰረት የከተማ አስተዳደሩ በተባባሩት ዓረብ ኢሚሬቶች መንግስት ድጋፍ አማካኝነት ከዋዲ አልሲደር ኮመርሻል ኢንቨስትመንት ሊያቢሊቲ ኩባንያ ጋር በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ68 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ በመጀመሪያ ዙር 30 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የውል ስምምነት ሰነድ መፈራረሙን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም ሌሎች ሁለት በመኖሪያ ቤት ግንባታ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ኩባያዎችን በቤት ልማት ዘርፍ ለማሳተፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጹት ወይዘሮ አዳነች÷ የውጭ ባለሀብቶች እና ገንቢዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ግንባታ ሲያካሂዱ ለሀገሪቱ አማራጭ የገንዘብ አቅርቦትን በማምጣት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 16 ዓመታት ከ300 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለነዋሪዎች የተላለፉ ሲሆን ÷ ከ139 ሺህ በላይ ቤቶች በግንባታ ላይ የሚገኙ እና ከእነዚህ ውስጥ 51 ሺህ በላይ ቤቶችን ግንባታ በፍጥነት አጠናቆ ለተመዝጋቢዎች ለማስተላለፍ ዝግጁ እየተደረጉ እንደሚገኙ ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.