Fana: At a Speed of Life!

ለእግር ኳስ ተጫዋቾች፣ አትሌቶች፣ ስፖርተኞች እና አርቲስቶች በ2013 ዓ.ም የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ገለጻ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሄራዊ የአረንጓዴ ልማት የ2013 ዓ.ም የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተካሄደ፡፡

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ የወንዶች እና ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አምበልና አባላት፣ አትሌቶች፣ ስፖርተኞች እና አርቲስቶች የተገኙ ሲሆን፥ በ2013 የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ችግኝ ተከላው ከዘር፣ ከፖለቲካ እና ከሃይማኖት የፀዳ በመሆኑ ሁሉንም አንድ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቶ ለቀጣዩ ትውልድ አረንጓዴ የሆነች ኢትዮጵያን ማስረከብ ይኖርበታልም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ በበኩላቸው፥ “ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ” መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አመታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተሳትፎ ሲያደርግ እንደነበር በማስታወስም የተተከሉ ችግኞችን እየተንከባከበ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

“አሁንም ሃላፊነታችን በጋራ እንወጣለን ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ አረንጓዴ አሻራችን በምናሳርፍበት ወቅት ህዳሴ ግድብን ከግምት ውስጥ ማስገባት” እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የዘንድሮው መርሃ ግብር “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን፥ አምናን ጨምሮ በአራት አመታት ውስጥ 20 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዟል፡፡

ለዘንድሮው አመትም 7 ነጥብ 7 ቢሊየን ችግኞች የተዘጋጁ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 6 ቢሊየን ችግኞች በሃገር ውስጥ ይተከላሉ ተብሏል፡፡

ከዚህ ባለፈም ከዲፕሎማሲ አንጻር በተመረጡ ስድስት ጎረቤት ሃገራት አንድ ቢሊየን ችግኞች ይተከላል ነው የተባለው፡፡

ለዘንድሮው ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የችግኝ ማፍላት ዝግጅቱ 11 ወራት የፈጀ ሲሆን፥1 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር መሬት ችግኝ መትከያ ቦታም ተለይቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም 21 ሺህ 600 ኩንታል ዘር ችግኞችን ለማፍላት ጥቅም ላይ ሲውል፥ ለችግኝ ዘር ግዥ 900 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ እስከ 23 ሚሊየን የሚጠጋ የህብረተሰብ ክፍል በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፈ ሲሆን፥ በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከዚህ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ህዝብ በማሳተፍ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ይሰራል ተብሏል፡፡

በዘቢብ ተክላይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.